ጸጋየ ገብረመድህን አርአያ በሚለው የብዕር ስሙ የምናውቀው አቶ ሙሉጌታ ሉሌ (ነብሱን ይማረውና ) በጦቢያ መጽሄት የሀምሌ 1998 እትም ላይ ባስነበበን ጽሁፍ “ በአስራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን ጭንቅላት የሀያ አንደኛውን ክፍለ ዘመን መግቢያ ችግሮቻችንን ለመፍታት የምንደፋደፍበትም ሁኔታ አለ ለማለት እደፈርለሁ፡፡ በዚህ የተነሳም ነው በዘመናችን የሀሳብ ትግልና የሰከነ ውይይት ብሔራዊ ርዕይ ሊሰርጽ ያልቻለው፣በ16ኛው ክፍለ ዘመን ጭንቅላት ማሰብ በዚህ የተነሳ በዚህ ሀገር በራሳችንም በመንግሥታችንም መተማመን እንደጠፋ እንኖራለን፡ የምናምንበትና ህሊናችንን የሚኮረኩር አንዳች ኃይል በማጣትም የመንፈስ ሽባነት ያደረብን ይመስላል፡፡ ”ብሎ ነበር፡፡
ይህ ጽሁፍ ለንባብ ከበቃ ዘጠኝ አመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም ዛሬም በትናንት አስተሳሰብ ስሜትና ፍላጎት በዛሬ ላይ ሽምጥ መጋለብ የሚቃጣቸው አሉና መልእክቱ አዲስ በመሆኑ ነው የታወሰኝና የጠቀስኩት፡፡በትናትት አስተሳሰብ ሲባል እድሜ አይወስነውም የ“ያ ” ወይም የ “ይህ” ትውልድ አባል መሆን አለመሆንም አይገድበውም፡፡ እድሜአቸው የትናንት አስተሳሰበቸው ከዘመኑ ጋር የሚዘምን የመኖራቸውን ያህል እድሜአቸው የዛሬ ሆኖ አስተሳሰባቸውም ሆነ ድርጊታቸው ከአባት አያቶቻቸው ዘመን ነቅነቅ ያላለ መኖራቸውን ራሳቸው ከሚናገሩት ከሚጽፉትና ቢችሉም ሊያደርጉ ከሚሞክሩት መረዳት ለይቶ ማወቅም ይቻላል፡፡
እንዲህ አይነቶቹ ሰዉን ሁሉ በእነርሱ የአስተሳሰብ መጠን የሚያዩ በመሆናቸው እነርሱ ወደ ብዙሀኑ በመምጣት ከዘመኑ ጋር ለመዘመን አይጣጣሩም፡፡እንደውም ራሳቸውን የሁሉ ነገር አዋቂና መፍትሄ አምጪ አድርገው በመውሰድ ሌሎች የሚያራምዱትን አስተሳሰብ ያጣጥላሉ፣እነርሱ ከሳሎናቸው ሳይወጡ በለውጡ መንገድ ክንድም ሆነ ርምጃ እየተጓዙ ያሉትን ይኮንናሉ፡፡ ከእነዚህ ጎን መሰለፍ ጅልነት በገንዘብ መርዳትም አላዋቂነት አንደሆነ አድርገው ይጮኸሉ፡፡
ከዚህ ሁሉ በላይ አሳዛኙ ቢቻልም አጠያያቂው እነዚህ በአብዛኛው ከሀገር አወጣጣቸው በምንም ይሁን በየት ኑሮአቸውን ከሀገር ውጪ ያደረጉ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የወያኔ በትር የማያርፍባቸው ወገኖች ሀገር ቤት እለት በእለት ፍዳ መከራውን እያ ባለው ህዝብ የፖለቲካ ቁማር ለመጫወት መከጀላቸው ነው፡፡ ህዝቡ የወያኔን ገዛዝ የተሸከመበት ጫንቃው ተልጦ፣ እህህ እያለ ኑሩ ቆሽቱን አሳርሮት፣ ሁሉ ነገር ከሚችለው በላይ ሆኖበት በቃኝ ብሎ አደባባይ ወጥቶ ጠመንጃ ከወደረ ኃይል ጋር በባዶ እጁ እየተጋፈጠ መስዋዕት ሲሆን የቁስለኛና የሙት ፎቶ በመለጠፍ ለሸቅል ሲጣደፉ ታዝበናል፡፡ የትግሉ አነሳሽ፣ የጉዞውም መንገድ ቀያሽ እነርሱ እንደሆኑ አድርገው ፕሮፓጋንዳ ሲነዙ በዚህም እኔ ነኝ እኔ ነኝ ሲወዛገቡ ሰምተን አጀኢብ ብለናል፡፡ ነገሩ “ሽልም ከሆነ ይገፋል ቦርጭም ከሆነ ይጠፋል” እንዲሉ ሆነና የህዝቡ ትግል ጋብ ሲል እነርሱም ድራሻቸው ጠፋ፡፡
ህዝቡ ሁሉንም ይታዘባል፣ ንግግርን ከተግባር እያነጻጸረ ይመዝናል፡፡ እነርሱ ግን በትናንት አስተሳሰብ ተጋርደው ዛሬም እንደ ትናንቱ በፕሮፓጋንዳ የህዝብን ድጋፍ ማግኘት ይቻል መስሎአቸው፣ ወያኔን መስደብና በአየር ላይ መፎከር ተቀዋሚ ያሰኝ መስሎአቸው፣በዘር መደራጀትና የጥላቻ ስብከት ደጋፊ የሚያበዛ መስሎአቸው የህዝቡን የማስተዋል ብቃት ከቁብ ባለመቁጠርና ትናንት ዛሬ አለመሆኑን ለመገንዘብ የሚያስችል አስተውሎት በማጣት በጀመሩት መንገድ ቀጥለዋል፡፡በቃልም ሆነ በጽሁፍ ከሚለገሳቸው ህዝቡም በተግባር ከሚያሳያቸው ለመማር የሚፈቅዱም አልሆኑ፡፡
ለማናቸውም አንቅሰቃሴ ውጤታማነት ጅምሩ ራስን፣ ጠላትን ሕዝቡን በሚገባ ማወቅ ላይ የተመሰረተ መሆን እንዳለበት ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡ የራስን ትክክለኛውን ወርድና ቁመት፣አቅምና ብቃት፣ወዘተ ማወቅ ካልተቻለ መነሻ ዓላማ፣ መድረሻ ግብ፣ ወደ ግቡ ማቅኛው መንገድ/የትግል አይነትና ሰልት፣ ተብሎ የሚዘጋጀው መነሻው ከራስ ትክክለኛ ማንነት የመነጨ ባለመሆኑ ከንቱ ነው ፡፡ ለዚህም ነው እንዳንዶች ወዴት እንደሚያመሩ ብቻ ሳይሆን ማንንና ለምን እንደሚታገሉ ለዳር ተመልካች ቀርቶ ለራሳቸው ግራ ሲጋቡ የሚታዩት፡፡
በአንጻሩ ከመነሻቸው ራሳቸውን በሚገባ አውቀው፣ ጠላታቸውን በቅጡ መዝነው፣ ህዝቡንም ተረድተው ትግሉን የጀመሩት ወገኖች የወያኔ አገዛዝ ያስመረረውና የድሉ ቀን የናፈቀው ሕዝብ በሚመኘው መጠን መንቀሳቀስ ባይችሉም የጉዞአቸው መስመር ለሁሉም በግልጽ ታውቋል ፣ ባቡሩሀዲዱን ተቆናጧል፣ አሽከርካሪው መሪውን ጨብጧል፡፡ ፍጥነት መዘግየቱን የሚወስኑ ውስጣዊም ውጫዊም ሁኔታዎች መኖራቸው አሌ የማይባል በመሆኑ የእውነተኛ ሀገር ወዳድ ነጻነት ናፋቄና ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊት ሀገር ሆና ለማየት የሚጓጓ ወይንም ለልጆቹ የሚመኝ ፍጥነቱን የሚያዘገዩ ነገሮችን ለማስወገድ በየሚችለው አቅም መረባረብ ነው ቅዱሱ ተግባር፡፡
በሰራተኝነት ቀርቶ በተጓዥነት እንኳን ባቡሩ ላይ ሳይሳፈሩ አረ እንደውም ባቡሩ የሚጓዝበት ሀዲድ የተዘረጋበትን መስመር አንኳን ሳያውቁ ( ለማዘግም ለመፍጠኑ አስተዋጽኦ አለውና) በርቀት ተቀምጦ ባቡሩ ለምን አይፈጥንም እያሉ መጠየቅ፣ ከዚህ አልፎም ለባበሩ ፍጥነት አንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ ተግባራትን ለመፈጸም መቃተት በምንም መመዘኛ ጤናማ ተግባር ሊሆን አይችልም፡፡ የግንቦት ሰባት አባል ነህ የሚል ከቁብ የማልቆጥረው ውርጅብኝ እንደሚገጥመኝ ባውቅም እዚህ ጋር አንድ ጥያቄ ልጠይቅ፣ ከሚስቱ እቅፍ ውስጥ ያልወጣ ወንድ ግንቦት ሰባቶች ለምን ውጊያ ገጥመው አያሳዩንም? ለምን አንድ ከተማ፣መንደር ኮረብታ ተቆጣጥረው የድል ከበሮ አይደልቁም? ወዘተ እያለ ጩኸት ሲያሰማ የወዳጅ ወይንስ የጠላት?
አብዛኛው ሰው ግን ባቡሩ ሀዲዱን መያዙን ጉዞም መጀመሩን በሚገባ ተረድቷል፡፡ወደ መዳረሻ ግቡ የሚደርሰበት የጉዞ ግዜ ማጠር መርዘም የሚወሰነውም በአሽከርካሪውና በሌሎቹ ሰራተኞች እንዲሁም በተሳፋሪዎቹ ትጋትና ፍላጎት ብቻ አለመሆኑን አውቋል፡፡ በመሆኑም ነው ለጉዞው አለመፍጠን ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮችን ለማስወገድ በሚችለው አቅም በእውቀቱ፣ በገንዘቡ፣ በጉልበቱ ወዘተ የተሰለፈው፡፡ እግረ መንገድ እዚህ ጋር አንድ ነገር ልበል፣ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ሕዝቡ ትብብሩን እያሳየ ነው፣ እየተባበረ ነው፣ ወዘተ የሚለው አገላለጽ የትግሉን ባለቤት ሌላ ስለሚያደርገው ተገቢ ሆኖ አልታየኝም፡፡ የተሳትፎው ደረጃ ምንም ይሁን ምን የነጻነት ትግሉ ዋንኛ ባለቤት ህዝቡ ነው፡፡
ሰሞኑን በ42 የተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በአንድ ቀን ለአርበኞች ግንቦት ሰባት ያካሄዱት የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም አንደም ህዝቡ የትግሉ ባለቤት መሆኑን፣ ሁለትም ባቡሩ ጉዞ መጀመሩንና ለፍጥነቱ የእነርሱ አስተዋጽኦ አስፈላጊ እና ምን መሆኑን መገንዘባቸውን፣ ሶስተኛም መጽሀፍ ቅዱስ ከፍሬአቸው ታውቁአቸዋላችሁ እንዳለው ህዝቡ አርበኞች ግንቦት ሰባትን በተግባሩ መዝኖ አውቆ የተቀበለው እና አመኔታውን የቸረው መሆኑን ያረጋገጠ ነው፡፡
ይህ የህዝብ አመኔታ ለአርበኞች ግንቦት ሰባት አመራርና አባላት አንቅልፍ ነሺ አደራ ይመስለኛል፡፡ ድርጅቱ የሰው ስብስብ እንደመሆኑ መሪም ተመሪም ሁሉም እኩል የዓላማ ጽናት፣ የትግል ቁርጠኝነት ከራስ በላይ የማሰብ ብቃት በእኩል ባይሆንም በተመጣጠነ ደረጃ ይኖራቸዋል ብሎ ማሰብ አይቻልም፡፡ ነገር ግን በየግዜው ህዝቡ የሚያሳየው አመኔታና የሚያደርገው የትግል አስተዋጽኦ ለሁሉም በእኩል የሚታይና የሚሰማ እንደመሆኑ የድርጅቱ አባላት በተለይ በመጀመሪያው የትል ምዕራፍ ላይ የሚገኙት አደራውን በእኩል ስሜት መቀበልና ከዓላማየ ብዛነፍ፣ በአለማዊ ነገር ከጉዞየ ብደናቀፍ…..ብለው ለየራሳቸው ቃል ኪዳን በመግባት ተከባብረውና ተደጋግፈው ወደ ፊት በመጓዝ የህዝቡን የነጻነት ቀን ለማፋጠን መጣር ይገባቸዋል፡፡
በአንጻሩ ግልጽ የሆነ መነሻ ዓላማ፣ መድረሻ ግብ፣ የትግል ምንነትና እንዴትነት የሌላቸውና ታጋይነታቸውን ወደ አርበኞች ግንቦት ሰባት የቃላት አረር በመተኮስ እያሳዩ ያሉ ወገኖች የህዝብ ድጋፍ እንዴትና በምን ሁኔታ አንደሚገኝ ከዚህ ከሰሞኑ ተግባር ቢማሩ የሚበጀው ለራሳቸው ነው፡፡ “ጨው ለራስህ ብለህ ጣፍጥ” እንደሚባለው ማለት ነው፡፡ እነርሱ በይህን ያህል ከተማ ቀርቶ በአንድ ከተማ አንኳን ስብሰባ ለመጥራት ምን ያህል እንደሚቸገሩ ከተሳካላቸውም ምን ያህል ሰው እንደሚገኝላቸው የሚያውቁት ነው፡፡ እድሜ ለዘመኑ የመገናኛ ቴክኖሎጂ በቅርብም በሩቅም ያለነውም ምስል ከድምጽ በተቀናበረ መረጃ ይደርሰናልና እናውቃለን፡፡
ቀና ልቡና ካለ፣ እውነተኛ ዓላማ ካለ፣ በርግጥ የሚታገሉት ለዴሞክራሲ ከሆነ፣ ይህ ራስን ለመፈተሽና አካሄድን ለማስተካከል ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ግን የተሳካውን በሰይጣናዊ ቅናት ማየት፣ ላልተሳካው ሰበብ ምክንያት መደርደር ለማንም ሳይሆን ለራሳቸው ለባለቤቶቹ አይበጅም፡፡ ስኬት የተግባራዊ ሥራ ውጤት ነው፡፡ በቅስቀሳ ብቻ ህዝብን ማነሳሳት፣ በፕሮፓጋንዳ ብቻ ድጋፍ ማግኘት፣ ወያኔን በማውገዝና በመስደብ ብቻ ተቀዋሚ መባል ዛሬ ግዜው አይደለም፡፡
ህዝቡ በዚህ መንገድ ብዙዎቹን አምኖ ተከትሎአቸው መሀል መንገድ ጥለውት ተቀይሰዋል፣ ኪሱን እያራቆተ ረድቷቸው በየመድረኩ እየተገኘ አጨብጭቦላቸውና ከእናንት ወዲያ ታጋይ ለአሳር ብሎ አሞግሶ አክብሮአቸው የተናገሩትን ሆነው ሊያገኛቸው አልቻለም፡፡እናም ሕዝቡ ከትናንት በበቂ ተምሯልና ዛሬ መመዘኛው ቃል ሳይሆን ተግባር ነው፡፡ እናም የህዝቡን ድጋፍ ለማግኘት ወሳኙ ነገር በተግባር መገኘት ነው፡፡ አርበኞች ግንቦት ሰባትም ይህ የህዝብ አመኔታ እየጠነከረ እንጂ እየላላ እንዳይሄድ አሜኔታ ያተረፈበትን ምክንያት መረዳትና አጥብቆ መቀጠል ይኖርበታል፡፡
በመጨረሻም፣ከምር ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን መሆን የምትታገሉ ወገኖች ከትናንት በስቲያና ትናንት እናንተም ሆናችሁ የቀደመው ትውልድ ያራመዳችሁት አስተሳሰብም ሆነ የሄዳችሁበት መንገድ ወደ ግባችሁ ማድረስ ቀርቶ በትክክለኛው መቃረቢያ መንገድ ላይ እንዳላቆማችሁ ተገንዛባችሁ የዛሬ ችግር በትናንት አስተሳሰብ፣ የዛሬ ጉዙ በትናንት ማጓጓዣ አንደማይሳካም ከራሳችሁ ልምድ ተምራችሁ ከዘመኑ ጋር ለመዘመን ነገ ሳይሆን ዛሬ፣ በዝግታ ሳይሆን በፍትነት መለወጥ ጀምሩ፡፡ ያ ሲሆን ለምንና ማንን አንደምትታገሉ፣ጥርት ብሎ ይታያችኋል፣ከራስ በላይ በማሰብም በሀገር ጉዳይ በዴሞክራሲ ጉዳይ ከማንም በተግባር ከሚንቀሳቀስ ጋር ሁሉ ለመተባበር የሚገዳችሁ አትሆኑም፡፡ ይሄ ሆነ ማለት ደግሞ የነጻነታችን ቀን ቀረበ ማለት ነው፡፡ ፈጣሪ ለዚህ ይርዳን፡፡
በጥቅስ እንደገባሁ ሁሉ በጥቅስ ልውጣ፣ አብርሀም ሊንከን ናቸው አሉ የተናገሩት “አንድ ዛፍ ለመቁረጥ 6 ሰአት ብትሰጠኝ 4ቱን ሰአት መጥረቢያ በመሳል አሳልፋለሁ፣2ቱን ሰአት ለመቁረጥ፡፡” መጥረቢያ ሳትይዙ ዛፍ መቁረጥ የሚያምራችሁም ሆናችሁ የዶለዶመ መጥረቢያ ይዛችሁ እየደከማችሁ ያላችሁ ይህች የአብርሀም ሊንከን የተሞክሮ ውጤት የሆነችውን አጭር አባባል በአንክሮ ብታጤኗት፡፡