Saturday, June 24, 2017

ጣራው ለሚያፈስ ቤት – የወለል እድሳት

መላ አከላቷን ዝንጀሮ እሾህ ወግቷት
መቆም መራድ መቀመጥ ተስኖአት
የትኛውን እንንቀልልሽ ብለው ቢጠይቋት፣
ብታስቀድሙልኝ የመቀመጫየን
እኔ እነቅለዋለሁ ቁጭ ብዬ ሌላውን፣
በማለት መለሰች
ቅድሚያ የሚሰጠውን ነገር ስላወቀች፡፡
ጣሪያው በሚያፈስ ቤት ውስት እየኖሩ ክረምት በመጣ ቁጥር እየተሰቃዩ በጋ  ሲሆን የወቅት መለዋወጥ የተፈጥሮ ባህርይ መሆኑ ተዘንግቶ ነገር አለሙን በመርሳት ወለሉን ቢያድሱት ግድግዳውን ቀለም ቢያብሱት አይቀሬ ነውና ክረምት ሲመጣ የሚሆነውን አስቡት፤ከንቱ ልፋት አጉል ብክነት፡፡
የቤቱ ወለል እድሳት ቢሻ፣ ግድግዳው ቀለም ቢያምረው፣ ጣራው ደህና እስከሆነ ድረስ መኖር አይከለክልምና ቅድሚያ መቀመጫየን እንዳለችው ዝንጀሮ መቀመጫን አስተካክሎ ሌላ ሌላውን በሂደት ቀን ሲፈቅድ አቅም ሲጎለብት ማደስ ይቻላል፡፡ ጣሪያው የሚያፈስ ቤት ውስጥ እየኖሩ ክረምቱ አልፏል ብሎ ወለል ማደስ ቅድግዳ ቀለም መቀባት ግን አንድም ሞኝነት ሁለትም አጭበርባሪነት ነው፡፡እንዲያም ሲል ከዛሬ ያለፈ አለማሰብ ይሆናል፡፡በአን ጎራ ካለነው እኛ ከምንባለው እነማን ከየትኛው ጎራ እንደሆኑ  እናንተው አስቡት፡፡
ሀገራችን ቤታችን ናት፤ ጣራዋ በብልሽትም በእርጅናም ተበለሻሽቶ በበጋ ለጸሀይ ሀሩር፣ በክረምት ለዝናም ዶፍ ብንዳረግም  ለምደን ተላማምደነው  እንኖራለን፡፡ገዢዎቻንም የእኛ ቻይነት፣ የፈረንጆቹም ጩኸት እንዴትነት ገብቷቸው ወለሉን እያደሱ፣ ግድገዳውን ቀለም እየቀባቡ  ለአላፊ አግዳሚውም ሆነ ለደርሶ ሀጅ ጎብኝው ችግሩ አንዳይታወቅ አንደውም ያማረ የሰመረ መስሎ አንዲታይ በማድረግና መኖሩን ችለውበታል፡፡ ያማረው ቤታችን ሞንዳላው ኑሮአችን እያሉ በሚያሰሙት ፕሮፓጋንዳም እኛን እያደነቆሩም አቀጣጫ እያሳቱም ከፈረንጆቹ ጋር እየተሞዳሞዱ ረብጣው ሳይነጥፍባቸው፣ ዲፕሎማሲያዊው ድጋፍ ሳይቋረጥባቸው፣ሲገድሉና ሲያስሩ የሚሰማው ተቃውሞም ከቃል ወደ ተግባር ሳይሸጋገርባቸው ሀያ ስድስት ዓመት እንደዋዛ ገዙን፡፡ ሁሉንም ነገር አይተው ገምተው ጠብ- መንጅቸውንም ተማምነው ገና አርባ አመት አንገዛችኋለን እያሉ ነው፡፡ ይበሉ! የታገሉት ለምንና ለማን ሆነና፡፡ ጥያቄው እኛ የምንባለው ከተቃውሞው ጎራ ያለነው ብዙ እኛዎች ያለፈውን የሰሩትን እያየን የወደፊት ምኞት ዝግጅታቸውን እየሰማን ምን አልን ምንስ አደረግን ነው ? ብዙዎቻችን ካለንበት ነቅነቅ ያላልነው  ከመማረር ወደ ማምረር ተሸጋግረን  ራሳችንን ከሰቀልንበት ከፍታ አውርደን ከመጯጫህ ወጥተን  አገዛዝ በቃን በማለት  የምንችለውን ጠጠርም ቢሆን ለማስቀመጥ ዝግጁ ነን ወይ? ነው ጥያቄው ይህ ካልሆነ ወያኔ ከምኞት ፍላጎቱም በላ ይገዛናል፡፡ አንደ አያያዛችን ከሆነ ብዙዎቻችን በአፋችን እንጮሀለን እንጂ በወያኔ የተፈጸመው ነገር ሁሉ ውስጣችን ዘልቆ አልተሰማንም ለዚህም ነው ከመማር ወደ ማምረር መሸጋገር ያልቻልነው፡፡ ይህ ባይሆንማ ኖሮ ወቅት እየጠበቀ ወያኔ በሚሰጠን መጫወቻ ከአንልፋችን እየባነንን በምናሰማው ውግዘት ጩኸት  ጣሪያው ለሚያፈስ ቤት የወለል እድሳት የምንጠይቅ ባልሆነ ነበር፡፡ በእኔ እምነት ጣራው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ነው፡ እንደ አብርሀም ሊንከን አባባል የህዝብ፣ በህዝብ፣  ለህዝብ፣  የሆነ መንግሥት ፡፡ ስለሆነም ይህ በሌለበት/በተነፈግንበት/ ሀገራችን  ሌሎች የህግም በሉት የሰብአዊ መብት፣ የቋንቋም በሉት የሀይማኖት ጥያቄዎችን ማንሳት  ታሰርን ተሰደድን ተገደልን እያሉ መጮህ ከሂደቱ ለማትረፍ እንጂ ከግቡ ለመድረስ የማንታገል ያስመስላል፡፡
ዴሞክራሲ ቅንጦት ተደርጎ በሚታይበት አገዛዝ ውስጥ እየኖሩ ስለ ቋንቋ፣ስለ ሀይማኖት፣ስለ ብሄር ብሄረሰብ፤ስለ ህግ በላይነት፣ስለ ሰብአዊ መብት መከበር ስለ ነጻ ምርጫ ወዘተ ማሰብ፣  መጠየቅ፣ መጮህ ጣራው በሚያፈስ ቤት እየኖሩ ወለል ለመቀየር ግድግዳ ለማደስ የመንደፋደፍ ያህል ነው፡፡ እነዚህ ጥያቄዎች ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ሲሆን ምላሽ የሚያገኙ ናቸው፡ ብቻ ሳይሆን ያለ እነዚህ ተግባራዊነት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሊኖር ስለማይችል ወያኔ በሥልጣን ለመቆየት ጠመንጃውን እንደሚተማመን ሁሉ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ ለሥልጣን የሚበቃ ግለሰብም ይሁን ፓርቲ እነዚህን ነገሮች ማክበርና ማስከበር የህልውናው ጉዳይ ይሆናል፡፡ ስለሆነም ከፈረሱ ጋሪው የሆነውን መያዣ መጨበጫ ያጣውን ነገራችንን በማስወገድ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እውን ማድረግ በሚያስችለው መንገድ አንደየአቅማችን እንራመድ፡፡ለዚህ ደግሞ ቀዳሚው ነገር ራስን መለወጥ ነው ፡፡ እዚህ ላይ አንድ ዘመን ተሸጋሪ አባባል ብጠቅስ ማለት የፈለኩትን ይበልጥ የሚያሳይልኝ መሰለኝና እነሆ!
የአሜሪካፕሬዝዳንት የነበሩት አብርሀም ሊንከን ለኮንግረስ ያስተላለፉት ሁለተኛው መልዕክታቸው ተብሎ በሚጠቀሰው ንግግራቸው «አንድ ትውልድ ያልፍና ሌላ ትወልድ ይተካል፣ ዓለም/መሬት ግን ለዘለአለም ትኖራለች፡፡ ጸጥ ረጭ ያለው ያለፈው ግዜ ፍልሰፍናዎች (ዶግማስ) አውሎ ነፋሳዊ ለሆነው ለዛሬው ችግር ለመፍትሄነት አይመጥኑም፡፡ ጊዜያችን ችግር ያዘለ ስለሆነ በአዲስ ሁኔታ ማሰብና በአዲስ ሁኔታም መንቀሳቀስ አለብን፡፡ ራሳችንን ከሰቀልንበት ከፍታ ማውረድ ይገባል፡፡ ያን ግዜ አገራችንን ለማዳን እንችላለን፡፡ ታሪክን ልናመልጥ አንችልም፣ልንሸሸው አይሆንልንም፣ ክፉም ሰራን ደግ እንዘከራለን፣ (እንታወሳለን) ግለሰባዊ መታወቅ ወይም አለመታወቅ አንዳችንንም ሆነ ሁላችንን አያተርፈንም፣የምናልፍበት እሳታዊ ፈተና (ፍርድ) በክብር ወይንም በውርደት ማለፋችንን ይመሰክራል»
ብዙዎች እኛ ፤ እነርሱ ወያኔዎች ምንም በሉዋቸው ምን ባነገቡት ዓላማ ሊደርሱበት በሚያስቡት ግብ አንድ ናቸው፡፡ በዚህ ጉዳይ አይደለም ሰው ነፋስ አያስገቡም፡፡እንዲህም በመሆናቸው ነው ታግለው ያሸነፉት፣ ሀያ ስድስት ዓመታትም በዙፋኑ ለመዝለቅ የበቁት፡፡ በተቃውሞው ሰፈር ያለነው እኛ ግን ብዙ እኛዎች ነን፡፡ ሰንደቅ ኣላማ ለብሶ ከሚፎክረው፣ ኢትዮጵያ እያለ ከሚዘምረው፣ የብሄር ኩታ ለብሶ ከሚያቀነቅነው ፖለቲከና አይደለሁም እያለ ከሚሸውደው  ወዘተ ብዙ እኛዎች መካከል  የቤታችን ጣራ ተቀይሮ ሁላችንም የጸሀዩ ሀሩር ሳጠብሰን፤ የክረምቱ ዝናም ሳያበሰብሰን መኖር የምችልበት ቤት እንዲኖረን ምን ያህሉ ነን ከምር የምንሻው ተብሎ ቢጠየቅ  ከብዙዎቹ ተግባር በማየት የምናገኘው ምላሽ አሉታዊ ነው የሚሆነው፡፡ ይህ ለወያኔ ግዞት ያመቻቸን መሰረት አልባው ልዩነታችን መሰረት የለሽ በመሆኑ ለገላጋይ ዳኛ ለመካሪ ሽማግሌም የሚመች አይደለም፡፡ ብዙዎች በቤታችን ጣራ መቀየር በየግላቸው ያምናሉ፣ነገር ግን ይህን እምነት የጋራ ለማድረግ ይቸገራሉ፣ለምክንያትነት የማይበቃው ሰበባቸው የሚያሳብቅባቸው ደግሞ ጣራው እኔ በምለውና በምፈልገው መንገድ ካልሆነ በስተቀር ባይለወጥ ይቅር የሚሉ ከራስ በላይ የማያስቡ መሆናቸው ነው፡፡ በግልጽ ቋንቋ ለመናገር እኔ አባዋራ የማልሆንበት ቤት አንኳን ጣራው ግድግዳውም ይደርመስ የሚሉ ነው የሚመስሉት፡፡
አንዳንዶቹ ደግሞ ለስሙ ከተቃውሞው ጎራ ከትመዋል እንጂ አድራጎት ንግግራቸው የተቃውሞ አይደለም፡፡ ጣራው እያፈሰሰም ለጸሀይ እየዳረገም ቢሆን ወለሉ ከታደሰ ግድጋዳው ቀለም ከተቀባ ርካታ የሚሰጣቸው አይነት ናቸው፡፡ ያ ባይሆን  ከሀያ ስድስት አመታት አገዛዝ በኋላ ዛሬ ስለ ህግ በላይነት፣ ስለ ሰብአዊ መብት መከበር፣ ስለ ሀብት እኩል ተጠቃሚነት፣ ስለ ፍትህ ወዘተ ለወያኔ  ማላዘኑ በቆመ ነበር፡፡ እነዚህ ከእባብ እንቁላል እርግብ የሚጠብቁ ሊባሉ የሚበቁ ይመስለኛል፡፡ ሌላው ሁሉ ቢቀርና ቢረሳን  የህዝቡ ጥያቄ ትክክል ነው፣ የሰጡትን ዝም ብሎ የማይቀበል ጠያቂ ትውልድ ፈጥረናል ወዘተ ብለው ተመጻድቀውና ተሳልቀው ለተቃውሞ መውጣቱም ሆነ ያነሳው ጥያቄ ትክክል ነው ያሉትን ህዝብ በገፍና በግፍ አስረው እያስተማርነው ነው ተሀድሶ እየሰጠነው ነው ከሚሉ ሰዎች ምን ሊገኝ ጥያቄ እንደሚቀርብ ጩኸት እንደሚሰማ አይገባኝም፡፡
እያዩያ አለማስተዋሉ፣እየሰሙ አለማዳመጡ፣ እያነበቡ አለመገንዘቡ በእኛ ሰፈር በመብዛቱ እንጂ ወያኔዎች ከጅምሩ በመቃብራችን ላይ ሲሉ በግልጽ ነግረውናል፡፡ጽፈው አስነብበውናል፣ በተለያየ መንገድ በዘፈንም በፊልም አሳይተውናል፡፡እኛ ሰፈር ግን በምኒልክ ዘመን የደነቆረ ምንይልክ ይሙት እንዳለ ይኖራል እንደሚባለው ሆነን በወያኔ ድል ማግስት የተጀመረው ጩኸት፣ልመና ተማጽኖ፣ ስድብ ዘለፋ የመግለጫ ተቃውሞ  ወይ መሻሻል ሳይሳይ ወይ አርጅቶ ገለል ሳይል እስካሁን አለ፡፡
ሎሬት ጸጋየ  ገብረ መድህን የአባቶቻችን ነገር ሳስታውሰው ትዝ የሚለኝ ከሞከርነው ነገር ይልቅ ያልሞከርነው ነው የሚቆጨኝ እንዳለው  እስከ ዛሬ የመጣንበት የፖለቲካ ጨዋታ አላዋጣም፣ የያዝነውም ተለይይቶ ጉዞ  ከምንለው ቦታ የሚያደርስ አልሆነም ስለዚህ ራሳችንን ፈትሸን፣ አመጣጣችንን ገምግምን ድክት ጥንካሬአችንን ለይተን፣ለዘመኑ የሚስማማውን አስተሳሰብ እንያዝ፣ ለትግሉ የሚመጥነው መንገድ እንከተል በማለት የሚታትሩ ብቅ ሲሉ ከወያኔ ሰፈር ባልተናነሰ ጩኸቱ የሚበዛውም ሆነ  ትንሽ ትንሽ መሰናክል ማስቀመጥ የሚጀመረው እኛ ከምንባለው ብዙዎቹ እኛዎች በኩል ነው፡፡
ቤቱ ጣራው ዝናብ ቢያፈስም፣ ጸሀይ ቢያስመታም ወለሉ ካማረ፣ ግድግዳው ቀለም ከተቀባባ ለእኔ ይመቸኛል፤ የጣራው ነገር አያስጨንቀኝም ማለት መብት ነው ምርጫ ነው፡፡ ለዴሞክራሲ ነው የምታገለው የሚል ሁሉ ይህን ምርጫ መቀበል የሰዎቹን መብት ማክበር ይገባዋል፡፡እነርሱ ደግሞ ጣራው መቀየር አለበት ብቻ ሳይሆን ካልተቀየረ በቤቱ ውስጥ መኖር አንችልም በሚለው ወገን እየተከለሉም እየተመሳሰሉም እያደናገሩም መኖሩን አቁመው አቋማቸው ጥቅም የሚያገኙበት ሳይሆን ከልብ የሚያምኑበት ከሆነ   መብታቸውን በይፋ መጠቀም እምነታቸውን በግልጽ ማራመድ ይኖርባቸዋል፡፡መሸፋፈን ለመኝታ ግዜ ብቻ ይሁን፡፡ ማለባበስ ይቁም!
በጣም አስቸጋሪው መፍትሄ አጥቶ የግዞት ዘመናችንን እያራዘመው ያለው በጣራው መቀየር ላይ ልዩነት ሳይኖር መቀየር ያለበት እኔ በምለው መንገድ ብቻ ነው የሚለው አስተሳሰብ ነው፡፡የነገሩ ክፋት የሚብሰው ደግሞ የዚህ አስተሳሰብ አራማጆች በሚሉት መንገድ ለመቀየር ስንዝር የተግባር እንቅስቃሴ የማያደርጉ መሆናቸው ነው፡፡ተግባሩ ቀርቶ እንዴት በምን ሁኔታ በማን ጣራው መለወጥ እንደሚችል ግልጽ አቋም የላቸውም፡፡ አቋማቸውን ገልጸው መንገዳቸውን አሳይተው ሊደርሱበት የሚያልሙትን ግብ ነግረው ደፋ ቀና በሚሉት ላይ ለመዝመት ግን እንቅልፍ የላቸውም ፡፡እንዲህ መሆን የለበትም፣ አንደዚህ ለምን ይደረጋል፣ በዚህ መንገድ ለምን ይኬዳል ከማለት በስተቀር እንዲህ ይሁን በዚህ መንገድ መሄድ ያዋጣል ወዘተ በተግባር ቀርቶ በቃል ደረጃ እንኳን አይናገሩም፡፡
ግልጽ አቋም በጣራው መለወጥ ላይ፣ የቤታችን ጣራ ከተለያየ አቅጣጫ ብዙ ስም የወጣለት ገዢዎቻችንም ሊያደናብሩንና አቅጣጫ ሊያስቱን በከጀሉ ቁጥር አዳዲስ ስም እያወጡ  በአንድ ያልረጉበት ሲሆን የምንሻው ግን ግልጽ ነው፡፡ዴሞክራሲያዊ ጣራ፡፡ ወራጅና ማገሩ ቆርቆሮና ምስማሩ በህዝብ ለህዝብ የህዝብ ሆኖ የሚሰራ ጣራ፡፡ይህን የሚጠላ ወይንም የማይፈልግ በአንደበቱ ባይናገረውም በተግባሩ እንለየዋልን፡፡የመጀመሪያው ወያኔና በዙሪያው ተኮልኩለው ተጠቃሚ የሆኑት ናቸው፡፡ለጥቆ የምናገኛቸው ሀያ ስድስት አመት ሙሉ ተቀዋሚ መባል ያልሰለቻቸው ምን አልባትም የሚያኖራቸው ወያኔ ተሰናብቶ ዴሞክራሲያዊ ሥርኣት ቢሰፍን ወለሉ ይታደስ ግድግዳው ቀለም ይቀባ አይነት የይስሙላ ተቃውሞ እያሰሙ መኖር አይችሉምና የጣራውን ለውጥ አይፈልጉትም፡፡ ሲስልስ ወያኔን ከማውገዝና ከማጥላላት ባለፈ የተጀመረም ሆነ የተሰነቀ ነገር የማይታይባቸው ነገር ግን ይህንኑ መኖሪያቸው ያደረጉ እናት ኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ብሉኮ ብትከናነብ ህዝባችን ተገደለ ታሰረ በዘራችን ብቻ ተጠቃን  እያሉ ነሸጥ ሲያደርጋቸውም በመገንጠል እያስፈራሩ፣ ሰከን ያሉ እለት ደግሞ ስለ አንድነት እየዘመሩ ያሉ፣ የሚኖሩ ወገኖች ያኔ ይህን ማድረግ አይችሉምና በአፋቸው የሚናገሩት/የሚነግዱበት  ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በተግባር እውን ሲሆን ለማየት ይሻሉ ብሎ ማሰብ ይቸግራል፡፡
በድርድርም በሉት በግርግር፤በሰላማዊ ሰለፍም በሉት በጩኸት፣በጽሁፍም ይሁን በንግግር የሚቀርቡ ጣራውን በመለወጥ ላይ የማያተኩሩ ነሮች ሁሉ ጣራው ለሚያፈስ ቤት የወለል እድሳት የመፈልግ ያህል ነውና ሲብስም እቅጣጫ የሚያስት ትግል የሚያዘናጋ ለገዢዎች እፎይታ የሚሰጥ ወዘተ ነውና ይታሰብብት፡፡ በሁሉም መንገድ በየትኛውም መስመር ትግል ጣራውን ለመቀየር፡፤

Monday, June 12, 2017

ሰውም እንደ ጊንጧ (ይገረም አለሙ)

ጊንጥ በመስክ ላይ ሆና በድንገት አካባቢው በውኃ ይጣለቀለቅና ነብስ ውጪ ነብስ ግቢ ጭንቀት ውስጥ ትገባለች፡፡ህይወቷን ለማትረፍ የምትችልበት መንገድ  ፍለጋ ዙሪያዋን ስትቃኝ በቅርብ ርቀት ኤሊን ታያትና ኤሊ ሆይ! እባክሽ አንች ውኃ አያጠቃሽምና አድኒኝ፣ ጀርባሽ ላይ አድርጊና ከዚህ መአት አውጪኝ ብላ ትማጸናታለች፡፡ ኤሊም የጊንጥን ባህርይ  ታውቃለችና ማዳኑን አድንሽ ነበር ነገር ግን አንች የንክሻ አመል ያለብሽ ዘሮቼን በንክሻ የጨረሽ ነሽና ትነክሽኛሽ አይሆንም  ትላታለች፡፡ ጊንጧም በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆኜ  አድኒኝ ብዬ ለምኜሽ እንዴት እነክስሻለሁ አላደርገውም እባክሽ ህይወቴን ታደጊያት በማለት አጥብቃ ስትለምናት በዛ ሁኔታ ጥላት ለመሄድ ዔሊ ሆዷ አልጨቅን ስላለ ጀርባዋ ላይ አስቀምጣ ዳር ስታደርሳት ከውኃው መውጣቷን ከአደጋው መዳኗን ያረጋገጠችው ጊንጥ ትነክሳታለች፡፡ ኤሊም የፈራችው፣ የጠረጠረችው ንክሻ ሲደርስባት ምን ብለሽ ነበር እንዴት ትነክሽኛለሽ ስትላት የጊንጧ ምላሽ አዝናለሁ ላለመንከስ መተው አልቻልኩም አመሌ ስለሆነ የሚል ነበር፡፡
ዙሪያ ገባችንን ስንቃኝ፣ የሚጻፍ የሚነገረውን ስናይ እንደ ጊንጧ አመል ሆኖባቸው አለያም ስራቸው ሆኖ ክፍያ የሚያገኙበት ወይንም በሎሌነት አድርው ለጌቶቻቸው እጅ መንሻ የሚያቀርቡት  ካልተናከሱ መኖር የማይችሉ ብዙ ሰዎችን እናገኛለን፡፡ጊንጧ ዔሊዋን እንደነከሰቻት በአካል አግኝቶ መንከሱ ባይሆንላቸውም ካሉበት ሆነው ከሚስቶቻቸው ጉያ ተሸጉጠው አለያም ከማጀት ሳይወጡ ምላሳቸውን ስለው ብእራቸውን አሹለው ለምንና ማንን  እንደሚናደፉ እንኳን በውል ምክንያት ሳይኖራቸው የሚራመደውን ትንሽም ቢሆን እንቅስቃሴ የሚያደርገውን ሁሉ  በቃላት የሚናደፉ በብልግናቸው የሚወርፉ ብዙ ብዙ እያየን ነው፡፡ በተለይ የሀገር ቤቱ ትግል ሲያተኩስ የፖለቲካው መድረክ ሲሟሟቅ በተግባሩ እነርሱ የሉበትምና በመድረኩ ላይ በሚታዩት በመስኩ ላይ በተግባር በሚገኙት ወገኖች ላይ ይዘምታሉ ሎሌዎቻቸውን ያዘምታሉ፡፡ እንዲህ የሚያደርጋቸው ታዲያ አመላቸው ወይንም ቅናታቸው ወይንም ክፍያቸው ነውና ነክሰው ማድማት ነድፈው ጉዳት ማድረስ ባይችሉም  ግዜ እየጠበቁ ብቅ ከማት አይቦዝኑም፡፡
ከሚናገሩት ከሚጽፉት (ከዚህ የዘለለ ተግባር የላቸውም) ድርጊታቸው  ማረጋገጥ እንደሚቻለው እነዚህ የጊንጥ ባህርይ የተላበሱ ወገኖች  ከወያኔ ተስማምቶ አለያም ጎመን በጤና ብሎ የሚኖረውንም ሆነ እኔ ከደላኝ ምን አገባኝ አለም ደህና ሰንብች ብሎ የተኛውን ወይንም በአፉ ከማውገዝ በመግለጫ ከመፎከር ያለፈ እንቅስቃሴ የማያሳየውን መንደፍ አይደለም እስከ መኖሩም አያውቁትም፡፡ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪው ዓለም በጎሳም ሆነ በሀራዊ ስም የሚጠሩ ብዙ ድርጅቶች አሉ፣የራዲዮና የቴሌቭዥን ጣቢያዎችም እንዲሁ፣ ተዲያ ጊንጦቹ መንከስ መንደፉ ባይሆንላቸውም የቃላት አረራቸውን የሚተኩሱት የሀሜት አሉባልታ ናዳቸውን የሚለቁት በእነማን ላይ አንደሆነ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ ግን ለምን?
ይሄ ነው እንግዲህ  ንክሻቸው እንደ ጊንጧ አመል ስለሆነባቸው ነው ከማስባል ይልቅ ለዓላማ የሚፈጽሙት፣ በእቅድ የሚከውኑት ተግባር ነው ለማለት የሚያበቃው፡፡ አመል ከሆነ ከቆመው እንደውም የተኛው ነበር ለንክሻ የሚቀለው ለመንደፍ የሚመቸው፡፡ የእኛ የሰዎቹ ጊንጦች ግን የሚራመደውን እየተከተሉ፣ የሚንቀሳቀሰውን እያነፈነፉ ነውና ንድፊያ ንክሻቸው ጉዳት የማያደርሱ ከመሆናቸው አንጻር ንቆ መተው የሚቻል ቢሆንም የሚሰሩትን አያውቁትምና ይቅር በላቸው የሚባልላቸው ባለመሆናቸው ለይቶ ማወቁ፣ ነቅቶ መጠበቁና መጠንቀቁ ቢበጅ እንጂ አይከፋም፡፡
እነዚህ ወገኖች መገለጫ ተግባራቸው ተመሳሳይ አረ እንደውም አንድ ቢሆንም ከእነርሱ ማንነትና ከአሰማሪያቸው ምንነት አንጻር ሲታዩ ዘርፈ ብዙ ናቸው፡፡ ከፊሎቹ ለሥልጣን እድሜው መርዘም ያዋጣኛል የሚለውን ማናቸውንም ነገር ከማድረግ ወደ ኋላ የማይለውና ለዚህ ይበጀኛል ካለ ከዲያቢሎስም ጋር ቢሆን ከመስራት የማይመለሰው ወያኔ አሰልጥኖ የተለያየ ጥብቆ አልብሶና ርስ በእርስም እንዳይተዋወቁ አድርጎ  የተለያየ ተልእኮ ሰጥቶና ስራ መድቦ በሁሉም ቦታ ያሰማራቸው ናቸው፡፡ እነዚህ ግራ ቀኝ ማየት፣ ወደ ፊትና ወደ ኋላ ማመዛዘን፣ የሚያዩትን ከተሰጣቸው ስልጠና  ከተነገራቸውና በየጊዜው ከሚነገራቸው ነገር ጋር ማመሳከርና ማመዛዘን የማይፈቀድላቸው ከመነሻውም ይህን ማድረግ የሚያስችላቸውን የአእምሮአቸውን ክፍል የተሰለቡ ናቸው፡፡ ለዚህም ነው እንድ መቅረጸ ድምጽ የተጫነባቸውን እንደ ገደል ማሚቱ ወይንም በቀቀን የተነገራቸውን ከመናገርና ከመጻፍ ውጪ የሚሰጣቸውን ምላሽ መስማት የሚለገሳቸውን ምክር መቀበል የማይሆንላቸው፡፡ ስለሆነም ለእነዚህ ምላሽ መስጠትም ሆነ አተካራ መግጠም የእነርሱ አጯጯሂ በመሆን ተልእኮአቸውን ከማሳካት ባለፈ የሚፈይደው ነገር የለምና ለይቶ በማወቅ ንቆ መተው ሌላውም እንዲያውቃቸው ማድረግ ነው የተሻለ የሚሆነው፡፡
ሌለኞቹ እንዲሁ የየራሳቸው ዘርፍ አላቸው፣ ዋንኛ ሊባሉ የሚችሉት እነርሱ ሊሆኑ የሚመኙትን ግን መሆን ያልቻሉትን ሌሎች መሆን ሲችሉ፣ ትንሽ የፖለቲካው አየር ሲያተኩስና መሆን የቻሉት በየመድረኩ ሲታዩ በእውን በህልማቸው የሚቃዡለት የሚቃዡበትን የምን-ይልህ ቤተ መንግስትን የተቀደሙ እየመሰላቸው ከሰይጣናዊ ቅናት በሚመነጭ ምቀኝነት የሚያደርጉት ነው፡፡ ቤተ መንግሥቱ ቢቀር የዚህ ወይንም የዛ ድርጅት መሪ ተብለው በየደረሱበት  ጭብጨባ ሲነጉድላቸው፣ ብሩ ሲጎርፍላቸው፣ አንቱታ ሲቸራቸው ማየትን የሚመኙ ነገር ግን የሚመኙትን ሆኖ ለመገኘት  ለዛ የሚያበቃ ዝግጅቱም፣ ብቃቱም፣ ቁርጠኝነቱም፣ ወዘተ የሌላቸው ሆኖ ሳይሳካላቸው አመታትን ያስቆጠሩ ሌሎች በተግባር እንቅስቃሴያቸው የህዝብ አክብሮት ሲቸራቸው ውዴታና ፍቅር ሲዘንብላቸው ለተግባራቸው ማስተግበሪያ ርዳታ ሲጎርፍላቸው አይናቸው ደም ይለብሳል፣ ጨጓራው በብሽቀት አሲድ ይረጫል፣ ይህን ተከትሎ እንደ ጊንጧ መናከስ መናደፍ እንደ መንደር አውል አሉባለታ ማውራት ስድብና አሽሙር መንዛት ወዘተ ስራቸው ይሆናል፡፡ ብዙ ርቆ መሄድ ሳያስፈልግ ያለፉትን ሁለት አመታት ለአፍታ መለስ ብለን በእክሮ ብንቃኝ በዚህ መስመር የተሰለፉትን ሰዎች ለይቶ ማውጣቱ ብዙም የሚቸግር አይሆንም፡፡ በተለይ ማህበራዊ መገናኛውን የመጠቀሙም የመበለቱም አቅሙ ላላቸው፡፡
በዚህ ጎራ ያሉት ሌሎቹ  ስልቻ ቀልቀሎ ቀልቀሎ ስልቻ ዝም ብለሽ ተቀበይ የሰጡሽን ብቻ አይነቶች ናቸው፡፡ ከላይኞቹ ጋር የተዛመዱበት ወይንም የታጠበቁበት ምክንያት ባይታወቅም ከእነርሱ የሚነገራቸውን ብቻ እየተቀበሉ በሉ በተባሉት ልክና መጠን የሚጮሁ ከቻሉም የሚናደፉ ናቸው፡፡ ስለሚናጋሩትም ሆነ ስለሚጽፉት ምንነት፣ ስለሚሳደቡት ሰውም ሆነ ድርጅት ማንነት ቀርቶ ስለሚያሰማሩዋቸው ሰዎች ዓላማን ግብ ተልኦኮና ድርጊት መረዳት ቀርቶ  በመጠኑ እንኳን የማያውቁ  አለማወቃቸውም ደንታቸው የማይሰጣቸው ናቸው፡፡ እንደ ሰው ሲያስቡት ሰው ዝም ብሎ የሚጮህ (ምን እንበለው)? ሲሆን  አሳዛኝም አሳፋሪም ነው፡፡ ህሊና የሚባልን ትልቅና ታላቅ ነገር እንዲህ እንደ አልባሌ እቃ አውጥቶ ማስቀመጥ ይቻላል እንዴ! ውሻ እንኳን ባለቤቱ ጃስ ሲለው እንዲነክሰው ጃስ የተባለበትን ሰው የሚያውቀው ከሆነ በባለቤቱና በሰውየው መካከል ሆኖ ግራ በመጋባት ስሜት ጅራቱን በማወዛወዝ ይቆማል የጌታው ትእዛዝ ቢበረታበት ግፊቱ ቢያይልበት ወደ ሰውየው ዞር እያለ በለሆሳሳ  ይጮኻል እንጂ ለመናከስ አይጋበዝም በጌታው ትእዛዝ ተደፋፍሮ ሰውየው ላይ ልከመር አይልም፡፡ እንዴት የሰው ልጅ ከዚህ ያንሳል፡፡
ባለቅኔው ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን እንዲህ መያዣ መጨበጫ ያጣው የተቃውሞው ጎራ ነገር ግራ ቢገባው የሚነገረው የሚሰራው እንቆቅልሽ ቢሆንበት እንዲህ ብሎ ነበር፡፡
«እኛ ምሁራን የምንባለውና ተቀዋሚ ፖለቲከኞች እሚባሉት ጭምር የዓለም ህብረተሰብ እንቆቅልሽ ነን፡፡ ለስሟ መጥሪያ ቁና ሰፋች ብቻ ነን፣ህዘቡን ርስ በርሱ እያጨፋጨፍን በዲስኩርና በድርሰት ብቻ አፍ ስንካፈት እያንዳንዳችን በሀቀኝነት የህዝቡ ወገን ሆነን የምንቆምበት ጀንበር እየጠለቀብን ነው፣ እንቆቅልሽ ነን፡፡» ጸጋየ በአካል ከተለየን አሰራ አምስት አመታት አልፈዋል፡፡ የባሰ እንጂ የተሻለ ነገር የለም፤ እንቆቅልሻችን እንዲህ ፈቺ አጥቶ ይልቁንም ተባብሶ ተመሳጥሮ ነገሩ ለከት አጥቶ ቢመለከተው ምን ይል ነበር፡፡
ይሄ እንቆቅልሻችንም መሰለኝ ጌትነት እንየውን እኛው ነን ብሎ ስንኝ ለመቋጠር ያበቃው፡፡
ካሳለፍነው ህይወት ካለፈው መከራ
መማር የተሳነን ደመና ወራሾች፣
የሞትነውም እኛ ያለነውም እኛ
ከፋይም ተቀባይ እኛው ነን ባለእዶች፡፡