April 17, 2014
ሰማያዊ ፓርቲ በመንግስት የሚፈጸሙ ሕገ ወጥ ድርጊቶች የሠብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብት ጥሰቶች እንዲቆሙ ለመንግስት አካላት በተደጋጋሚ ጊዜያት ጥሪ ማቅረቡ የሚታወስ ነው፡፡

ይሁን እንጂ መንግስት እነዚህን ተከታታይ ጥሪዎች ተቀብሎ የማሻሻያ እርምጃ ከመውሰድና ችግሮችን ከመቅረፍ ይልቅ ጉዳዩን ችላ በማለት ችግሮቹ የበለጠ እየተባባሱ እንዲሄዱ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
በመሆኑም እነዚህ ችግሮች በአስቸኳይ እንዲፈቱ ለማድረግ ሰማያዊ ፓርቲ እሁድ ሚያዚያ 19/2006 ዓ.ም ከጠዋቱ 4 ሰዓት እስከ 8 ሰዓት የሚቆይ ከፓርቲ ጽ/ቤት እስከ ጃን ሜዳ የሚደርስ ታላቅ ህዝባዊ የተቃውሞ ሰልፍ ያዘጋጀ ሲሆን የሠላማዊ ሰልፉን ቀንና ሰዓትም በአዋጅ ቁጥር 031983 መሠረት ለሚመለከተው አካል በደብዳቤ በማሳወቅ ሰልፉን ለማድረግ በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡
በዚህ ታላቅ ሕዝባዊ ሰልፍ ላይም ከዚህ ቀደም ተነስተው የነበሩ መንግስት በእምነት ጣልቃ ገብነቱን እንዲያቆም፣ ዜጎችን ከቀያቸው ማፈናቀሉ እንዲቆምና ዜጎቹ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ እንዲደረግ የሚሉ ጥያቄዎች የሚነሱ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም ለገዢው ፓርቲ ስልጣን እንጂ ለህዝብ የማይጨነቁት ተቋማት ስራቸውን በሚገባ ባለመስራታቸው ሕዝብ ለከፈለው ክፍያ አገልግሎት እያገኘ አለመሆኑም የወቅቱ አሳሳቢ ጉዳይ ሲሆን በተለይ የውሃ የመብራት የቴሌ ኮሚኒኬሽንና የትራንስፖርት አገልግሎቶች ሕዝብን እያማረሩ መሆናቸው በሠላማዊ ሠልፉ ላይ የሚነሱ ወሳኝ ጥያቄዎች ናቸው፡፡
በመሆኑም ይህን ታላቅ ሠላማዊ ሠልፍ የተሳካ እንዲሆን ለማድረግ የተነጠቁ መብቶቻችንን እናስመልስ ዘንድ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ሲቪክ ማህበራትና ሚዲያው ከሚደረገው ጥረት ጎን በመቆም ሀገራዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ ጥሪያችን እናስተላልፋለን፡፡
ሚያዝያ 2006 ዓ.ም
አዲስ አበባ
አዲስ አበባ
No comments:
Post a Comment