Monday, December 1, 2014

ዘረኛውና አምባገነኑ የህወሓት አገዛዝ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ከካድሬ ማሰልጠኛ ማዕከላትነት ለይቶ የማያይ ስለመሆኑ በተቋማቱ ውስጥ የሚደረጉ ተግባራት ማረጋገጫዎች ናቸው። ለዚህ ተግባሩ በሰነድ ደረጃ መቅረብ ከሚችሉት የቅርብ ጊዜ ማስረጃዎች ዋነኛው በህዳር 2007 ዓ.ም. በሥራ ላይ የዋለው “የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የኢህአዴግ የምርጫ ድል ልማት ሰራዊት ግንባታ አደረጃጀት ማንዋል” የተሰኘው በትምህርት ሚኒስቴር ተዘጋጅቶ ለሁሉም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተላለፈው ሰነድ ነው። ይህ ሰነድ፣ የህወሓት አሳፋሪ የትምህርት ፓሊሲ ባፈጠጠ መልኩ የተገለፀበት፤ የኢፌዴሪ መንግሥት ተብሎ በሚጠራው የህወሓት አገዛዝ ተቋም እና በህወሓት/ኢህአዴግ ፓርቲ መካከል ለይምሰል እንኳን ልዩነት አለመኖሩ በግላጭ የሚታይበት ሰነድ በመሆኑ በዚህ ርዕሰ አንቀሳችን በስፋት ልንዳስሰው ወስነናል። ሰነዱ በትምህርት ሥርዓቱ ላይ መርዙን መርጨት የሚጀምረው ገና በመግቢያው ስለማንዋሉ አስፈላጊነት ሲገልጽ ነው። ማንዋሉ “ከምንም በላይ የብጥብጥና የሁከት መንስኤ የሆነውን ተማሪ በኢህአዴግ አመራር አባላት እየታገዙ ለመያዝ የሚያስችል ነው” በማለት ህወሓት ተማሪውን የሚመለከተው “ከምንም በላይ በብጥብጥ መንስኤነት” መሆኑ፤ ለዚህ መድሀኒቱ ደግሞ ተማሪውን በኢህአዴግ አመራር አባላት “መያዝ” መሆኑን በማያሻማ ሁኔታ ይገልፃል። ቀጥሎም “በምርጫው ሊፈጠር የሚችለውን የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ሁከትና ብጥብጥ ለማስቆም በማደራጀት መረጃ ለመጥለፍ አመችነቱ የላቀ እንደሚሆን ታምኖበታል” በማለት መረጃ መጥለፍ የዩኒቨርስቲዎችና የትምህርት ሚኒስቴር ሥራ እንደሆነ አድርጎ ያቀርባል።

የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አስራት አብርሃን ጨምሮ ከአርባ በላይ የሚሆኑ የፓርቲው አባላት ቃሊቲ እስር ቤት ውስጥ ታገቱ፡፡አንድነት ፓርቲ የሚሊዮኖች ድምፅ ለህሊና እስረኞች በሚል መሪ ቃል ከህዳር 14 ጀምሮ እያካሄደያለው የማህበራዊ ሚዲያ ንቅናቄ አካል የሆነውን የህሊና እስረኞችን የመጎብኘት መርሀ-ግብር ለመሳተፍ ወደ ቃሊቲ እስር ቤት ያቀኑት የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አስራት አብርሃ እና የፓርቲው የአዲስ አበባ ሰብሳቢ አቶነገሰ ተፋረደኝን ጨምሮ 40 የአንድነት ፓርቲ አባላት ለግዜው ምክንያቱ ባልታወቀ ሰበብ በእስር ቤቱ ግዜያዊ ማቆያ እንዲገቡ መደረጋቸውን የፍኖተ ነፃነት ምንጮች ከስፍራው ዘግበዋል፡፡ አንድነት የሚሊዮኖች ድምፅ ለህሊና እስረኞች በሚል መሪቃል በዚህ ሳምንት እያካሄደ ያለው ንቅናቄ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያንን ትኩረት ማግኘቱ ገዢውን ቡድን ማስቆጣቱ መዘገቡ ይታወሳል፡፡

No comments:

Post a Comment