RADIO & TV

OPPOSITION PARTIES

NEWS & VIEWS

Wednesday, August 19, 2015

የወንዝን ውኃ የሚያጮኸው እውስጡ ያለ ድንጋይ ነው (ይገረም አለሙ)

የወንዘ ውኃ የውሀው መጠን ጨመረም ቀነሰም ለጥ ባለ አሸዋማ ሜዳ ላይ ድምጹ ሳይሰማ መሰሰ ብሎ ነው የሚሄድ፡፡ ከውስጥ ድንጋይ ያለበት አካባቢ ደግሞ ትንሽ ዝናብ ሲጥልና መጠኑ ሲጨምር ውኃው ከድንጋይ ድንጋይ እየተላጋ ጩኸቱ አካባቢውን ይረብሻል፡፡
ሰውም አንዲሁ ነው፡፡ እርር ድብን እያለ በንዴት እየነደደ በእልህ እየተቃጠለ፤ ብበሶት እየተብሰለለሰለ በቁጭት እየተንገበገበ በቅናት እያረረ ( በእነዚህ በአንዱ ወይንም ከአንድ በላይ በሆነ ምክንያት) የሚናገር የሚጽፍ ከንግግሩ አነጋገሩ፣ ከመጻፉ የቃላት አጠቃቀሙ ስሜቱን ስለሚያጋልጥበት ይህ አባባል ይጠቀስበታል፡፡
መቼም አይዘጋ ጆሮ በር የለው አንዲሉ ሆኖብን ከቅርብ ግዜ ወዲህ አንዳንድ ሰዎች የሚናገሩትን ስንሰማ፤ከድረ ገጽ ድረ- ገጽ እየተንጎዳጎድን የሚጽፉትን ስናነብ የወንዙን ውኃ እንደሚያስጮኹት አይነት ቋጥኞች በውስጣቸው መኖራቸውን ታዘብን፡፡ እነዛ ቋጥኞችም ቅናት፣ ምቀኝነት፣የተበለጥኩ ስሜት ፣ ጥማችንን ተነጠቅን ማለት፣ ጥላቻ፣ከእኔ ወዲያ ባይነት ወዘተ ናቸው፡፡TPLF/EPRDF political operatives
በቃልም ሆነ በጽሁፍ እንደሚነግሩን ከሆነ ከእነዚህ ሰዎች አንዳንዶቹ ከአመታት በፊት ኤርትራ ሄደው አቶ ኢሳይያስን እጅ ነስተዋል፣ በርሀ ወርደው የአርበኞች ግንባር አባላትን አግኝተዋል፡ አስመራ ላይ ከሻዕቢያ ባለሥልጣናት ጋር ተዋውቀዋል፡፡ አውሮፓና አሜሪካ ተቀምጠው በርሀ ባለው አርበኛ ከሚነግዱና በሀገርና በህዝብ ላይ ከሚቆምሩ ሰዎች ጋርም ወዳጅነት መስርተዋል ( እነሱም ቆማሪ ወይም አቋማሪ የነበሩ ይመስላል፡፡)
ወደ ኤርትራ ያማምራታቸው ምክንያት አርበኞቹን ሊያጠናክሩ ትግሉንም ሊመሩ መስዋዕትነት ለሚጠይቀው ትግል ቆርጠውና ተዘጋጅተው አንዳልነበር የትናት ድርጊታቸውም ሆነ የዛሬ ዋይታቸው በበቂ ይመሰክራል፡፡ ታዲያ ካልሆነ ኤርትራ ድረስ ምን አስኬዳቸው ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ በርግጥ አላማቸው ታጋዮቹን አደራጅቶ ትግሉን መርቶ የኢትዮጵን ሕዝብ ከወያኔ አገዛዝ ማላቀቅ ቢሆን ኖሮና ያሰቡት የደከሙበት በተለያየ ምክንያት ከሽፎ ከሆነ ዛሬ ያ ትግል ሲቀጣጠል ሊደሰቱ እንጂ አንዲህ እርር ድብን ሊሉ ባልተገባ ነበር፡፡ እናም ይህ የሚያሳየው አስመራ ድረስ የደከሙት፣ በርሀ ወርደን ነበር የሚሉት ከትግሉ በስተጀርባ የከወኑት ነገር መኖሩን ነው፡፡ ያ ደግሞ አሁን በራሳቸው አንደበትና ድርጊት እየተጋለጠ ነው፡፡
ያልነበረ ትግል እየቦተለኩ(በሀገሬ ሰው አባባል ቦተለከ ማለት ዋሸ ማለት ነው) ኢሳይያስን እየካቡ፣ አርበኛውን የማያውቁትንና እርሱም የማያውቃቸውን አውሮፓና አሜሪካ የሚኖሩ ነጋዴዎች (በትግሉ የሚነግዱ) ስመ መሪዎች ጋር እየተሞከሻሹ አገር አማን ብለው ከአሜሪካ አስመራ የዘረጉትን እቅድ በማሳካት ላይ ሳሉ አንዳርጋቸው ጽጌ ድንገት እነርሱ ደረስን ያሉበት ቦታ ሁሉ ደርሶ አርበኞችን አሰባስቦ ከግንቦት 7 ጋር አዋሀደ፤ ከኢሳይያስ ጋር ተደራድሮ ለትግሉ መነሻ ቦታ መንደርደሪያ ጥሪጊያ አመቻቸ፣ እናም የጥቂቶች መነገጃ ሆኖ የነበረውን ትግል ብዙሀኑን ነጻ ወደሚያወጣ የእውነትና የምር ትግል ለወጠውና የመሸቀያ(መነገጃ) ካርዳቸውን አሳጣቸው፡፡ ይህ አበሳጭቶአቸው ጸጉራቸውን ሲነጩ አንዳርጋቸው ተያዘና እፎይታ ተሰማቸው ተረጋጉ፡፡
ከእንግዲህ የትም አይደርሱም ብለው የተነጠቁትን ካርድ በእጃቸው አንደሚያስገቡ ርግጠኛ ሆነው ለዚሁ ያበቃናል ባሉት ስራ ላይ ሲንደፋደፉ ሁለት የኢሳት ጋዜጠኞች እነርሱ ሄደንበት ነበር ከሚሉት ቦታ ተገኝተው ያዩትን በምስል የሰሙትን በድምጽ ይዘው በመመለስ ለአለም ሲናኙት በተበለጥንም በተቀደምንም ወይ ነዶ ስሜት ተቃጠሉ፡፡በቅናት አረሩ፤በጥላቻ በገኑ፡፡
የወንዙ ውኃ በውስጡ ባለ ድንጋይ እንደሚታወከው ሁሉ እነዚህም ሰዎች በውስጣቸው ባቆጠቆጠ መጥፎ ስሜት መንፈሳቸው ታውኮ በአንደበታቸውም በብዕራቸውም ጮኹ፤ በፊልም የሚታየው ውሸት በቃል የሚባለው ሁሉ የሌለ ነው፤ እኛ ሄደን አይተነዋል፣ በማለት የጋዜጠኞቹ ምስል ከድምጽ ዘገባ ተአማኒነት እንዳያገኝ ለማድረግ ተጠራሩ፣ጣሩ ተጣጣሩ፡፡ እነርሱ እጅ ሲነሱት መልአክ የነበረው ኢሳይያስ በአንድ ጀንበር ሰይጣን ተደረገ፡ አለኝታችን የተባለው ሻዕቢያ ጠላታችን ተባለ፡፡
የጋዜጠኞቹን የቃልም የምስልም ዘገባ በማጣጣል ተአማኒነት አሳጥተው የመሸቀያ ካርዳቸውን በእጃቸው ለማስገባት ሲጣጣሩ የጨዋታውን መጀመር ያበሰረው ፊሽካ ተነፋና አቅለው ብለው ቆለለው ሆነባቸው፤ ግን በዚህም ተስፋ አልቆረጡ መፈራገጣቸውን ቀጠሉ፡፡ የህልውና ጉዳይ አይደል እንዴት ተስፋ ይቆረጣል፡፡ በዚህ ግዜ ደግሞ በቃ ከእንግዲህ ሰው ሰብስቤ ማውራት ላቆም ነው አሉና የንቅናቄው መሪ ሳይታቡ በድንገት የትግሉ ሜዳ ዱብ አሉ፡፡ ከታጋዩቹ መካከል ተገኙ፡፡ቃል ተግባር ሆነ፡፡
አሁን የመጨረሻው መጨረሻ መጣ፡፡ አንዳንዶቹ ከዚህ በላይ ለመሄድ ወይ የራሳቸው ህሊና ወይ ምን እንባላለን ፍርሀት አላስቻላቸውም፡፡ ባለማወቅ የተወናበዱና ነገሩ የምር ያልመሰላቸው ፊሽካው ሲነፋ አመራሮቹ ከጨዋታው ሜዳ ሲገኙ በአደባባይ ይቅርታ ባይጠይቁም ፈጣሪያቸውን ይቅር በለን ብለው ደጋፊ ሆነዋል ወይንም መቃወማቸውን አቁመዋል፤የቆማሪዎች አቋማሪ ከመሆንም ራሳቸውን አቅበዋል፡፡
ጥቂቶቹ ደግሞ እቅዳቸው መሰናከሉ የገቢ ምንጫቸው መድረቁ እየታያቸው በተበለጠን ስሜት፡ጥቅማችንን ተነጠቅን በሚል ቁጭት፣እኛ በወጣን በወረድንበት በሚል ቅናት በጥላቻ ስሜት ወዘተ መንፈሳቸው ከወዲያ ወዲህ እየተላጋ መያዣ መጨበጫ በሌለው ጩኸታቸው ቀጥለዋል፡፡
እነርሱ የዛሬ ምናምን አመት ኤርትርያ ተገኝተው ያነሱት ፎቶ ለመሸቀያ፣ ዛሬ የሚነሳው ፎቶ ግን ለትግሉ ማቀጣጠያ ሲውል አያችሁት ያ ከእገሌ ጎን የሚታየው እገሌ የሚባል የሻዕቢያ ሰው ነው፡ እነዛ በስተግራ በኩል ያሉት ደግሞ የእገሌ ድርጅት ታጋዮች ናቸው ወዘተ እያሉ ሊያስረዱን ሞከሩ፡፡ መቼም አጀኢብ የሚያሰኙ ናቸው፡፡አስመራ የተገኘን አንግዳ የሀገሪቱ መንግሥት ባለሥልጣን ሊቀበለው በግዛቱ ችግር እንዳይገጥመውም ሊጠብቀው ግድ ነው፡፡በኤርትራ ምድር ከሻዕቢያ አትገናኙ ማለት ..፤
የሉም የተባሉት አርበኞች ኖረው፣ ውሸት የተባለው ትግል በተግባር ከመታየት አልፎ በአካባቢው ከሚገኙ ሌሎች ድርጅቶች ጋር ትግሉን የማስተባበር ስራ ሲጀመር በተለይ ከዴምህት ጋር ከትብብር አልፈው አንድ ወደ መሆን የሚያደርሳቸውን መንገድ ሲያያዙ ዴምህት የትሮይ ፈረስ ነው አሉ፡፡ ራሳቸው አንደነገሩን ይህ ድርጅት ከተቋቋመ እነርሱም ሲያውቁት በርካታ አመታት አልፈዋል፡፡ የትሮይ ፈረስነቱ የታያቸው ግን አሁን ነው ፡፡ እንደው ለመሆኑ ዴምህት የትሮይ ፈረስ ነው ሲሉ በሱ ተከልሎ ወይም ተደብቆ የሚጓዘው ማ ሊሆን ነው፤ ሻዕቢያ ወይንስ በግል ኢሳይያስ? ምንስ ለመሆን? ምንልክ ቤተ መነግሥት ለመግባት ወይንስ አስመራ ተቀምጦ ኢትዮጵያን ቅኝ ለመግዛት? አድማጭ አንባቢ ካገኙ ጩኸታቸው የሚቆም አይመስልም፡፡
በቅዱስ መጽኃፍ ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች በጻፈው መልእክት ም.6ቁ 3 “አንዱ ምንም ሳይሆን ምንም የሆነ ቢመስለው ራሱን ያታልላልና..” ተብሎ እንደተጻፈው እነዚህ ምንም ሳይሆኑ የሆኑ መስሎአቸው የአቀዱት እቅድ በመክሸፉ ተንገብግበው የሚጮኹ ሰዎች ከመቃወም በቀር አማራጭ መንገድም ስልትም ማሳየት አልቻሉምና ከእንግዲህ ራሳቸውን ያታልሉ ካልሆነ ማንንም ሊያታልሉ አይሆንላቸውም፡፡
ውስጣቸው ያለው ቋጥኝ ቋጥኝ የሚያክል መጥፎ ስሜት በጠበልም ሆነ በዱአ በባህላዊም ሆነ ዘመናዊ ህክምና የማይወገድ መሆኑ አንጂ ቢፈወሱ ምን እየሰሩ አንደሆነ ራሳቸውን በታዘቡት ነበር፡፡ አንዴ ገብተውበታልና ከአፈርኩ አይመልሰኝ እያሉ በቀጠሉ ቁጥር ይበልጥ እየታወቁ አላማ ፍላጎታቸው እየተጋለጠ ጆሮአቸውን አምነው ያጀቡዋቸው አይናቸውን እያመኑ እየራቁዋቸው ብቻቸውን ይቀራሉ፡፡ የራስ ጥቅም ከሀገር በላይ ሆኖባቸው ቅናትና ጥላቻ አውሮአቸው ነውና በጥፋት ላይ የተሰማሩት፤ መካሪም ነጋሪም ሳያጡ አልሰማ ብለው ነውና ከበሰበሱ አይቀር ጭቅይት ብለው የቀጠሉት እነርሱ አያሳዝኑም ፡፡ የሚያሳዝኑት ልጆቻቸው ናቸው፡፡የእገሌ ልጅ መባል አለና፡፡
በቅዱሱ መጽፍ በሐዋርያት ሥራ ም.5 ቀ 38/39 “ይህ ሀሳብ ወይም ሥራ ከሰው አንደ ሆነ ይጠፋል ከእግዚአብሄር እንደ ሆነ ግን ታጠፉአቸው ዘንድ አይቻላችሁም ፣በእርግጥ ከእግዚአብሄር ጋር ስትጣሉ ምናባት እንዳትገኙ፡” ተብሎ አንደተጻፈው የኢትዮጵያውያን ለቅሶ ከፈጣሪ ደርሶ የጭቆና ዘመናችንን ሊያስጥረው እሱ አንድዬ ወስኖ እነ ብርሀኑን ለውሳኔው አስፈጻሚነት መርጦአቸው ከሆነ የጥቂት ሰዎች ጫጫታ አይደለም የወያኔ ወታደራዊ ዘመቻም አይበግራቸው ፡፡
አበቃሁ፤ሀዘኑን ደስታውን፤ምኞቱን ተስፋውን ፤ምክር ግሳጼውን ወዘተ በመንዙማ (በእንጉርጉሮ) በመግለጽ የሚታወቀው ወሎዬ ከላይ የጠቀስናቸው አይነት ሰዎች ድርጊት ሲያጋጥመው “አላህ ሲቆጣ ብትር አይቆርጥም ያደርጋል እንጂ ነገር እንዳይጥም” ይላል፡፡
የሰው ልጅ ህሊናውና ሆዱ ቦታ ሲለዋወጡ በእውነት ላይ ይሸፍታል፤ ያኔ ከፈጣሪው ጋር ይጣላል፤ ፈጣሪ ደግሞ መቅጫ መንገዱ ብዙ ነው ፤አንዱ ወሎየው ወገኔ እንደሚለው ነገሩ እንዳይጥም ማድረግ ነው፤ ጎጃሜው ወገኔ ግምኛ የሚለው፡፡ ምክር አለመለሳቸውም ቁጣ አላስታገሳቸውም ምን አልባት በዚህ ቢሻላቸው ወገን ናቸውና አንደየሀይማኖታችን እንጸልይላቸው፡፡ ሆዳቸው ውስጥ ከተጎለተውና መንፈሳቸውን እያወከ የሚያስጮኸቸው ቅናት ምቀኝት ተበለጥኩ ጥቅሜን ተነጠቅሁ ወዘተ ስሜት ተላቀው ለሀገርና ለወገን የሚበጅ ተግባር ላይ እንዲገኙ፤ ካልሆነም ለራሳቸው የሰላም ኑሮ መኖር እንዲችሉ፡፡ የክፋት ስሜት ራሱን ባለቤቱን ነውና የሚጎዳው፡፡
መጽኃፍ ቅዱስም ይላል፤ “ቅንአትና አድመኝነት ባሉበት ስፍራ በዚያ ሁከትና ክፉ ሥራ ሁሉ አሉና ላይኛይቱ ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጽህት ናት፡፡ በኋላም ታራቂ፣ ገር፣ እሺ ባይ፣ ምህረትና በጎ ፍሬ የሞላባት ጥርጣሬና ግብዝነት የሌለባት ናት ፡፡ የጽድቅም ፍሬ ሰላምን ለሚያደርጉት ሰዎች በሰላም ይዞራል፡፡”” ያዕቆብ 3፣16-18)
ሁሉን በግዜው የሚያደርገው አንድየ የማሪያም ልጅ ለታጋዮቹ ብርታትን ለደጋፊዎች ጽናትን ለተቀዋሚዎች ልቦና ይስጠን፡፡

No comments:

Post a Comment