Monday, October 12, 2015

ምን ቢያሰማምሩት ብረት ወርቅ አይሆንም

አንድ ሰሞን ጉድ አሰኝቶ የነበረውን ብረት ወርቅ የመሆን ወሬ የምናስታውስ ይመስለኛል፡፡የአባትህ ቤት ሲበዘበዝ አንተም አብረህ በዝብዝ የሚለውን ብሂል ተከትለው በማጭበርበር ተግባር ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎችና የባንክ ሰራተኞች ተመሳጥረው ብረት አቅልጠው ወርቅ ቅብ ቀብተው ብሄራዊ ባንክ በክብር አስገብተው ብራቸውን ይዘው ላሽ አሉ፡፡ ነገር ግን ምን ቢያሰማምሩት ብረት ወርቅ ሊሆን አይችልምና፣ ከመጀመሪያውም ወርቅ ተብሎ ከወርቅ ተራ ሊቀመጥ የበቃው ለዝርፊያ በተባበሩ ሰራኞች ነውና ብረትነቱ ሲታወቅ ያለቦታው ከተቀመጠበት ተወገደ፤አምጪዎቹም አስቀማጮቹም መታደን ጀመሩ፡፡ ምን ያህሉ እንደተያዙ ምን ያህሉ እንዳመለጡ እንጃ እንጂ የተያዙ መኖራቸው ይታወቃል፡፡
ይህን በምሳሌነት ያስነሳኝ የሰሞኑን የፓርላማ ውሎና የመንግስት አመሰራረት ነው፡፡ አንዳንድ ወገኖች ምን ጠብቀው ምን አንዳጡ ግልጽ ባልሆነ ሁኔታ አስተያየት ሲሰጡ ይታያል፡፡ ከመቶ በላይ ተቀዋሚ ፓርላማ ወንበር በያዘበት ወቅት ያልታየ ያልተሰማን ነገር ዛሬ መቶ በመቶ አሸነፍን ባሉበት ግዜ ምን ለማየት ምን ለመስማት ተጠብቆ ነው፤ የጠቅላይ ምኒስትር አሰያየሙ የአፈ ጉባኤዎች አመዳደቡ የፕሬዝዳንቱ ንግግር ብሎም የእንደራሴዎች ማንቀላፋት ቁም ነገር ሆኖ ሊነገር ሊጻፍ የሚበቃው፡፡
አንዳንዶች ደግሞ የምኒስትሮችን ሹም ሽረትና ቦታ መለዋወጥ ከቁም ነገር የቆጠሩት፤ ለአምስት አመት እቅዴ ቡራኬ ስጡልኝ በማለት ለተቀዋሚዎች ያቀረበውን የውይይት ጥሪም የመለወጥ አድርገው የወሰዱት ይመስላል፤ ምን አልባት ወያኔን አሁንም ከሀያ አራት አመት በኋላ በቅጡ ያለማወቅ ነገር ይኖር ይሆን? ወይንስ አጉል ተስፈኝነት፤ ወያኔን እንደ ብረቱ ምሳሌ ብንወስደው የቱንም ያህል ሰው ቢቀያይር የቱንም ያህል የማስመሰያና የማስቀያሻ ቃላት ቢደረድር የቱንም ያህል አምሮና ተኳኩሎ ብቅ ቢል አይደለም ወርቅ ብር ሊሆን አይችልም፡፡
የምኒስትሮች ምደባ የሚካሄደው ከመነሻው ለወያኔ አገልጋይነት ራሳቸውን አሳልፈው የሰጡ፤ ታማኝነታቸው የተረጋገጠ ታዛዥነታቸው የተመሰከረ ሰዎች ከየድርጅታቸው ተጠንተው የህውኃትን ይሁንታ አግኝተው በመሆኑ የአዳዲስ ሰዎች መምጣትም ሆነ የቦታ መለዋወጥ የሚያመጣው አንዳች ነገር ይኖራል ብሎ ማሰብ አንድም የዋህነት ሁለትም ወያኔን አለማወቅ ነው፡፡ እንደውም ይህ የሚያሳየው ወርቅ ተብሎ ብሔራዊ ባንክ እንደገባው ብረት ወያኔ በደንብ ተመሳስሎና ተቀባብቶ መምጣት ቢችል ወርቅ ነው ብለን ራሳችንን አታለን ወይንም ደልለን የምንቀበል እንደምንኖር ነው፡፡ ወያኔ ተፈጥሮው አይፈቅድለትምና አላደረገውም አንጂ ከተቀዋሚ ፖለቲከኞች አንድ ሁለቱን ምኒስትር አድርጎ ቢሾም (እምቢ ይሉ ይሆን ?) በቃ ወያኔ ተለውጧል ልንደግፈው አንጂ ልንቃወመው አይገባም የሚሉም አይጠፉም፡፡ ማደናገሪያው ሁሉ ካደናገረን፤ማስቀየሻው ሁሉ አቅጣጫ ካሳተን፣ማስመሰያው መንፈሻችንን ካላላው ከመነሻው ተቃውሞአችን መሰረት የለሽ ነበር ማለት ያስችላል፡፡
በየጊዜው በሚሰጠን ማደናገሪያ እየተደናገርን በማስቀየሻው አቅጣጫችንን እየሳትን የተባበረና የተጠናከረ የምር ትግል ማድረግ አለመቻላችንን የተገገነዘበው ወያኔ በየግዜው አዳዲስ የሚመስሉንን ግን አዲስ ያልሆኑ ነገሮችን ይሰጠናል፡፡ አሁንም አዲስ ነገር ይዞልን መጥቷል፡፡ ፓርላማው ተቀዋሚዎች ባይኖሩበትም ክርክር የሚካሄድበት፣ የህዝብ ድምጽ የሚስተጋባበት፣ የሀገር ችግሮች ለውይይት የሚቀርቡበት እንዲመስል ለማድረግ ማድረግን ያለመ ህግ ወጥቷል፡፡
ብርጫ 97 ተቀዋሚዎች በርካታ ወንበር ማግኘታቸው ሲታወቅ የተቀዋሚዎቹን አንደበት የሚለጉም የምክር ቤቱ የሥነ ሥርዓት መመሪያ የሚል ደንብ የሥራ ግዜውን በጨረሰው ተሰናባች ፓርላማ ወጣ፤ አንድ የተቀዋሚ ተመራጭ ፓርላማ በነበረበት አንድ የፓርላማ ዘመንም ያ ደንብ ሳይለወጥ ወይንም ሳይሻሻል በሥራ ላይ ቆይቷል፡፡ አሁን ግን መቶ በመቶ እነርሱ ብቻ ሲሆኑ በወያኔ የተያዘ ፓርላማ የሚለውን የተቃውሞ ድምጽ ለማዳከምና አቅጣጫ ለማስለወጥ አዲስ ህግ አወጡ፡፡ እንደ አንዳንዶች አያያዝ ከሆነ ነገ ከነግ ወዲያ በዚህ ደንብ መሰረት ፍሬ የሌለው የይስሙላ ክርክር ሲካሄድ፤ ምኒስትሮች እየቀረቡ ሲጠየቁ ወዘተ ስናይ ስንሰማ ወያኔ ተለውጧል ልንል ነው ማለት ነው፡፡
ምንም ቢያደርግ ምንም ቢናገር ወያኔ ወያኔ ነው ያው የደደቢቱ፤ መሰረታዊ ለውጥ ለማድረግ ደግሞ ተፈጥሮውም እድገቱም አይፈቅድለትም፡፡ ስለሆነም ወያኔዎች የሚያደርጉትም ሆነ የሚናገሩት ቀልባችንን ሊስበው ግዜያችንን ሊሻማው አይገባም፡፡
የህዝብ እንደራሴ የሚል ስም ተሸክመው ፓርላማ ውስጥ ተደላድለው ሲያንቀላፉ ያየናቸውን ሰዎች አስመልክቶ ማዘንና ማፈር ያለብን በሰዎቹና በድርጅታቸው ሳይሆን ሀገራችን ለዚህ እንዳትበቃ ማድረግ ባለመቻላችን ለራሳችንና በራሳችን ነው፡፡ ጥቃት መሮን፤ አገዛዝ አንገሽግሾን ለጋራ ድል በጋራ መሰለፍ፤ በተናጠልም ቢሆን ከምር መታገል ባለመቻላችን የሚመከርበት ሳይሆን የሚተኛበት ፓርላማ ለማየት በቃን፡፡ በዚሁ ከቀጠልንና እድሜ ከሰጠን ነገ ደግሞ የባሳ እናያለን እንሰማለን፡፡ ስለሆነም ከወያኔ በኩል የሚሆን የሚሰማውን እንተወውና ሀገራችን ለእንዲህ አይነቱ አሳፋሪ ደረጃ ለመድረሷ የእኛ ድርሻ የለም ወይ ብለን እንጠይቅ፤ማድረግ ሲኖርብን ያላደረግነው፤ ማድረግ ሳይኖርብን ያደረግነውስ አለ ብለን እንመርምር፣ እኛ በዚሁ ከቀጠልን ወያኔ መቼም የሚሻሻል ባለመሆኑ የነገው ከዛሬ እንደሚብስ ተረድተን መነጋገርና መላ መምታት ያለብን በዚህ ላይ ነው፡፡
ወያኔዎች ፋኖነትና የሀገር መሪነት ፈጽሞ የተለያየ መሆኑን ተረድተው እንደ ተጋዳላይነት ሳይሆን እንደ መንግሥት መሪነት አንዲያስቡና አንዲሰሩ፤ በድርጅት ከተቀነበበ አስተሳሰብ ወጥተው ሀገራዊ አስተሳብ እንዲኖራቸው፤ከጉልበት ወደ እውቀት አመራር አንዲሸጋገሩ ወዘተ ለማስቻል ባለፉት ሀያ አራት አመታት በተለያየ ዘዴና መንገድ ብዙ ጥረት ተደርጓል፤ተጽፏል ተነግሯል፡፡ አንዱም ግን ሰሚ አላገኘም፤ እንደውም ምክር የለገሱ አስተያየት የሰጡ አቅጣጫ የጠቆሙ ውግዘት ዘለፋ ሲያልፍም እስርና ስደት ነው የተረፋቸው፡፡ስለሆነም ዛሬ ላይ ሆነን ካለፉ ሀያ አራት አመታት ድርጊቶቹ ወያኔን በደንብ አውቀን ተቀራራቢ ግንዛቤ ሊኖረን ካልቻለና በአንድ መንፈስና ጉልበት ካልተነሳን ሳብ ረገብ የሆነው ትግላችን ለውጥ የሚያመጣ ሳይሆን የወያኔን እድሜ ማራዘሚያ ነው የሚሆነው፡፡
ብረቱ የወርቅ ቅብ ተቀብቶ ለአጭር ግዜም ቢሆን ብሔራዊ ባንክ መግባት እንደቻለው ሁሉ የወያኔ ባለሥልጣናት የህዝብ ልብ ውስጥ መግባት ያስችለናል በሚል በንግግርም ሆነ በማስመሰያ ድርጊት ያልሆኑትንና የማይሆኑትን መስለው ቢቀርቡ እውነተኛ ማንነታቸውን ረስተን ወይንም ዘንግተን ልባችን ዷ የሚል ከሆነ ለከፋ አገዛዝ ራሳችንን እያመቻቸን መሆኑን ማወቅ ይኖርብናል፡፡ ምክንያቱም ወያኔ ያው ወያኔ ነውና፤ ያውም የደደቢቱ፡፡
ከምር ለውጥ የምንሻ ከሆነ፤ በአንደበታችንና በብዕራችን እንደምንናገረው ከምር ምሬት መሮን ከሆነ፤ ተቀዋሚ ለመባል ሳይሆን ከምር ነጻነት የምሻ ከሆነ ስለ ወያኔ ማንነትና ምንነት እንዲሁም ንግግርና ድርጊት ማውራት ይበቃናል፤ እስከ ዛሬ በተጻፈ በተነገረው ያልተባለ ልንለው የምንችለው አዲስ ነገር የለም መደጋገም ካልሆነ፡፡ አሁን በድፍረት በግልጽና በእውነት መጻፍም መናገርም መነጋገርም ያለብን ስለራሳችን መሆን አለበት፡፡ ወያኔ ሀያ አራት አመት የገዛው በሱ ጥንካሬ ወይንስ በእኛ ድክመት? በእኛ ድክመት መሆኑን ከተቀበልን ድክመታችን ምንድን ነው? ብለን እንነጋገር፡፡ የወያኔ መቶ በመቶ አሸናፊነት የማይቆጨን የኢትዮጵያ ፓርላማ መኝታ ቤት መሆን የማያሳዛን የማያሳፍረን ጋኖች ባሉበት ሀገር ምንቸቶች ጋን ሊሆኑ ሲንደፋደፉ የማይነደን ከአሁኑ የወደፊቱ ሊብስ መቻሉ የማያሳስበን፤ ስለምን ነው ብለን ይህን ለመለወጥ ምን ማድረግ ነው የምንችለው የሚገባንስ ብለን መነጋገርና መላ መምታት ካልቻልን የወያኔ ጥፋት ይቀጥላል፡፡
ፖለቲከኞችም የምናይ የምንሰማውን ብሎም በተግባር እየተፈጸምብንን የምናውቀውን መልሳችሁ ከምትነግሩን፤ ድክመታችሁን አርማችሁ ጥንካሬአችሁን አጎልብታችሁ ለመታገል ምን እያደረጋችሁ አንደሆነ ንገሩን፤ ሆድና ጀርባ አድርጎ አላስማማ ላችሁን ርስ በርስ ለመቀዋወም ያበቃችሁን ችግር ተነጋገራችሁ በመፍታት ከመግለጫ ተቀዋሚነት ወደ ተግባር ታጋይነት የሚያሸጋግራችሁን ጥንካሬ ፍጠሩ፡፡ የማትችሉ ከሆነም የልዩነታችሁን ምክንያት ደግፈን ምረጠን ለምትሉት ሕዝብ ግልጽ አድርጉ፤ ቢቻል ለማስማማት ካልተቻለም አጥፊውን አውቆ አስቸጋሪውን ለይቶ ለማግለል ይበጃል፤ለነገሩ እናነተ አታውቁትም እንጂ አብዛኛው ሕዝብ ያውቃችኋል፡አንቅሮ ሲተፋ ደግሞ ታውቁታላችሁ፡፡ አንዴ ከጠላ ጠላ ብቻ ሳይሆን ጣለ ነው፤
እገረ መንገድ አንድ ፤ ሴቶች የህብረተሰቡ ግማሽ ኣካል ናቸው ይባላል፤ ያለ ሴቶች ተሳትፎ ልማት አይታሰብም የሚል መፈክርም ይሰማል፤ ሴቶችን ማብቃት የሚለውም አንድ ሰሞን ዋንኛ የፖለቲካ አጀንዳ ሆኖ ስልጠና ስብሰባ፤ ወረክ ሾፕ ወዘተ እየተባለ ገንዘብ ማግኛ ሆኖ ነበር ወዘተ፤ ነገር ግን በህውኃት ተመድበው በአቶ ኃይለማሪያም ለፓርላማው ከተገለጹትና በዛውም ለሕዝብ ይፋ ከሆኑት ሰላሳ ያህል ምስትሮች ውስጥ የሚታየው የሶስት ሴቶች ስም ነው፡፡ እውቀትና ብቃት ሳይሆን ታማኝነትና ታዛዥነት መስፈርት ለሆነበት፤የሚያምኑበትን ሳይሆን የሚታዘዙትን ብቻ ለሚሰሩበት ሥልጣን ህሊናችንን አናቆሽሽም መንፈሳችንንም አናረክስም በማለት እህቶቻችን እምቢ አሉ ወይንስ “ መቶ በመቶ በሆነ ድምጽ ከተመረጠው፤ ገጠር ከከተማ ሰው ሁሉ የእሱ አባልና ደጋፊ ከሆነው” ከወያኔ ሰፈር ከሶስት ሴት በስተቀር ለኢህአዴጋዊ ምኒስትርነት የሚበቃ ሴት ጠፋ፤
ሁለት፤ ማናቸውም ጉዳይ በመጀመሪያ በአራቱ አባል በሚባሉት ድርጅቶች አልቆ ከዛም ኢህአዴግ በሚባለው የህውሀት ጭንብል ማረጋገጫ ተሰጥቶት ነው ወደ ፓርላማ የሚመጣው፤ በዚህ ሁኔታ ባለቀ ጉዳይ ላይ ፓርላማው ምንድን ነው የሚያደርገው፤የይስሙላ ውይይት ከዛም እጅ አውጥቶ በመሉ ድምጽ ማጽደቅ፤ ቢቀርስ፡፡ ሁሉንም ነገር አስቀድመው ስላወቁት የሚያዩትም የሚሰሙትም አዲስ ነገር ባለመኖሩ የሚቀሰቅስም የሚቆሰቁስም ተቀዋሚ ስለሌለ ይሆናል እንደራሴዎቻችን ገና ከጅምሩ ፓርላማ የተኙት፡፡ እውነታቸውን ነው ፡፡ ተሰበሰቡም አልተሰበሰቡ ተናገሩም አልተናገሩ በድርጅት ከተወሰነው በፓርላማ አንድ መስመር መለውጥ እንደማይቻል ማወቃቸው ይመስለኛል ያስተኛቸው፡፡ ታዲያ ምን አለ እነርሱም መሳቂያ ድርጅታቸውም ማፈሪያ ( የቅርታ ለካ ወያኔ ሰፈር ሀፍረት ኤታወቅም) ከሚሆኑ በየቤታቸው ቢቀመጡ፤ ወይ ጉድ ስለ ወያኔ ማውራት እናቁም እያልኩ ገባሁበት አይደል፤ ቸር እንሰንብት ምሬት ይምረረን ቁጭት

No comments:

Post a Comment