በሀገር ውስጥም በውጪም ቁጥራው እጅግ የበዛ ተግባራቸው ግን ብዙም የማይታይ ፓርቲዎች አሉ፡፡ እነዚህ የሚችሉት ተዋህደው አንድ በመሆን የማይችሉት ተባብረው ትብብርም ይሁን ግንባር በመፍጠር የነጻነት ቀናችንን ለማፋጠን የሚያስችል ትግል ያደርጉ ዘንድ ስንመኝ፣ስንጠይቅ፣ስንማጸን፣ይህን ባለማድረጋቸውም ስንኮንን ወዘተ አመታት ተቆጥረዋል፡፡ እነርሱ ግን መተባበሩ ቀርቶ መከባበሩ አልሆን ብሎአቸው፣ ተደጋግፎ መቆሙ ቢቀር አንዱ ለአንዱ እንቅፋት ከመሆን መቆጠብ ተስኖአቸው ወያኔ ያሻውን እንዳሻውና ባሰኘው መንገድና ግዜ እየፈጸመ ከዚህ እንዲደርስ አድርገውታል፡፡
ከፖለቲከኞቹ ትግል ይልቅ የተጠራቀመ ብሶት የቀሰቀሰው የህዝብ ቁጣ ወያኔን አንበርክኮት የአዲስ አበባና አጎራባች ከተሞች የተቀናጀ ማስተር ፕላን ያለውን ካልፈለጋችሁት ትቸዋለሁ፣ ካልወደዳችሁት አይተገበርም እስከማለት አድርሶታል፡፡ ፖለቲከኞቻችን ግን ከዚህም በቅጡ የተማሩም የተመከሩም አይመስልም፡፡ ለወራት የዘለቀው የህዝብ ተቃውሞ የታቀደ የተቀናጀና በአግባቡ የተመራ ቢሆን ምን ሊሆን ይችል ነበር፡፡
ይህ አያሌ ኢትዮጵያውያን የሞቱበት፤ የታሰሩበት፤ ቁም ስቀል ያዩበትና በትንሹም ቢሆን ፍሬ ያሳየ ትግል የተቃውሞ ጎራው ፖለቲከኞችም ከየመሸጉበት ብቅ ብቅ እንዲሉ አስችሏል፡፡ ነገር ግን ሁሌም እንዲህ አይነት ክስተት ሲፈጠር የሚያሰሙትን መተባበር አስፈላጊ ነው የሚል መግለጫቸውን ካሰሙን በኋላ ሕዝቡ በትግሉ ቀጥሎ እየሞተ እየታሰረ እነርሱ የሚታይ የሚሰማ ጉልህ እንቅስቃሴ አለማድረጋቸው መግለጫ ያወጡት በእምነት ወይንስ አለን ለማለት የሚል ጥርጣሬ የሚያጭር ሆኗል፡፡
ይህን ስል ከመግለጫዎቹ ማግስት ሰላማዊ ሰልፍ ለመጥራት የተባበሩትን፣ ወያኔ ለሱዳን መሬት ለመስጠት የያዘውን ሽር ጉድ በመቃወም ትብብር ያሳዩትን በመዘንጋት ሳይሆን ፖለቲከኞቹ እንታገልለታልን ከሚሉት ዓላማ፤ ሕዝቡ እየከፈለ ካለው መስዋዕትነትና ወያኔ የሥልጣን እድሜውን ለማራዘም ከሚሰራው አንጻር ከቁጥር የሚገባ ባለመሆኑ ነው፡፡
የወቅቱን የህዝብ አንቅስቃሴ ምክንያት አድርገው ለወያኔ አገዛዝ መርዘም ዋናው ምክንያት የተቀዋሚዎች አለመተባበር መሆኑን የተናገሩት ፖለቲከኞች ይህን ባሉ ማግስት ያለፈው ሁሉ አስቆጭቶአቸው ቃላቸውን ወደ ተግባር የማሸጋገር የምር ስራ መጀመር ነበረባቸው፡፡ ነገር ግን ይህ ነው የሚባል እንቅስቃሴ ሳይታይባቸው ወራቶች እየነጎዱ ነው፤ መተባበር የሚለው ጩኸትና መግለጫም እንደተለመደው የአንድ ሰሞን እየመሰለ ነው፡፡
የነገሩን የሚያምኑበትን ቢሆን፣ የተሰለፉበትን ትግል ከምር የያዙት ቢሆን፣የወያኔ አድራጎት ከምር አስቆጥቶአቸው ቢሆን፤ የእነርሱ የአመታት ድል አልባ ትግል ከልብ አስቆጭቶአቸው ቢሆን..ወዘተ መግለጫ ባወጡ ማግስት ተጠራርተው መተባበር አቅቶን የወያኔን እድሜ የምናራዝመው ስለምን ነው ብለው በሽታቸውን ለማወቅና መድሀኒት ለመፈለግ ተጣጥረው አንድ ነገር ባሳዩን ባሰሙን ነበር፡፡ድምጻቸውን አጥፍተው እየሰሩ ከሆነና ውጤት ላይ ሲደርሱ ሊነግሩን አስበው ከሆነ ደግሞ እሰየው የሚያሰኝ ነው፡፡
የፓርቲዎች ትብብር የተወሰኑ ሰዎች ተገናኝተው ኮሚቴ ወይንም ግብረ ሀይል አቋቁመው በሚያዘጋጁት ሰነድ ላይ ተመስርቶ የሚፈጠር ሳይሆን በሚተባበሩት ወገኖች እምነትና ግልጽ ውይይት የሚመሰረት መሆን አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ የሀያ ዓመት ተሞክሮአችን በበቂ ያሳየን ይመስለኛል፣ አልተማርነብትም እንጂ፡፡ ስለሆነም ቀዳሚው ተግባር የአገዛዝ ዘመናችንን ያራዘመንው እኛው ነን ባለመተባበራችን ብለው የሚያምኑ፣ከእንግዲህ በዚህ መልኩ የኢትጵያውያን የግዞት ዘመን መርዘም የለበትም ብለው የወሰኑ፤ ያለፈውን መርምረው የአሁኑን አጢነው መጪውንም ተንብየው በጋራ ለአስተማማኝና ዘላቂ ድል የሚያታግላቸው መርሀ ግብር ለመንደፍ የሚያበቃቸው ውይይት መጀመር ይኖርባቸዋል፡፡
ወይይቱ የሚፈለገው ውጤት ላይ እንዲደርስ መሰራት ያለባቸው ቀዳሚ ተግባራት፡፡
ፓርቲዎቹ የትግል ስልታቸው ምንም ይሁን ምን አደረጃጀታቸው ሁለት አይነት ነው፡፡ ብሔራዊና ሕብረ ብሔራዊ ወይም ክልላዊና ሀገራዊ ፡፡ ነገር ግን አደረጃጀታቸው ሀገራዊ ሆኖ የዓላማ ልዩነት የሌላቸው ብዙ ድርጅቶች አሉ፡፡ በተመሳሳይ አደረጃጀታቸው ክልላዊ ሆኖ እንወክለዋለን ከሚሉት ብሄረሰብ በስተቀር የዓላማ ልዩነት የሌላቸው በርካታ ድርጅቶችም አሉ፡፡ ከዚህም አልፎ በአንድ ብሄረስብ ስም የሚጠሩ ድርጅቶች አሉ፡፡እነዚህ የስማቸውም መመሳሰል እያስቸገረ በእገሌ የሚመራው ይሄኛው፤ በእገሌ የሚመራው የኛው እየተባሉ ሲጠሩ እየሰማንም ነው፡፡ እንግዲህ የፓርቲዎች ትብብር ሲታሰብ እነዚህ ሁሉ አንድ መድረክ ላይ እንዲገኙ ይፈለጋል፡፡ ኢትዮጵያ የሁሉችንም ናትና፤ ችግሩ የጋራችን ከቸግሩ መውጫ መንገድም የሁሉም የተባበረ ትግል ነውና፡፡
ነገር ግን የጋራ ትብብር ለመፍጠር በሚካሄደው ስብሰባ እነዚህ ሁሉ በአሉበት ደረጃ የሚካፈሉ ከሆነ ውጤታማ ሊሆን ስለማይችል አስቀድሞ እያንዳንዱ በየግሉ ቀጥሎም ተመሳሳይ የሆኑት በመገናኘት ሊሰሩት የሚገባ የቤት ስራ መኖር አለበት፡፡ ሁሉም የቤት ስራውን ሰርቶ ለትልቁ የጋራ ዓላማ ራሱን አዘጋጅቶና ከልብ አምኖ ወደ ዋናው መድረክ ከመጣ በአጭር ግዜ ውጤታማ ስምምነት ላይ መድረስና የተግባር አንቅስቃሴ መጀመር ይቻላል፡፡በመሆኑም፤
አንድ፤ ሁሉም ድርጅቶች በየቤታቸው፤ የአንድ ጎልምሳ እድሜ ያስቆጠሩትም ሆኑ የቅርብ ግዜዎቹ ሁሉም በየቤታቸው ግልጽ ውይይት በማድረግ ከተመሰረትን ጀምሮ ምን ሰራን; ለውጤት ያልበቃነው ለምንድን ነው ;እንደ ድርጅት ጠንክረን መውጣት ያልቻልንበት ምክንያት ምንድን ነው;ከሌሎች ጋር ለመዋሀድም ሆነ በትብብር ለመስራት የሚያግድን ምንድን ነው;ከዚህ በኋላ እንዴት ነው መቀጠል ያለብን;ወዘተ ለሚሉ ጥያቄዎች ግልጽና እውነተኛ መልስ መፈለግ፡፡
ሁለት፣ ህብረ ብሄራዊ አደረጃጀት ያላቸው፤እነዚህ በአደረጃጀትም በዓላማም ልዩነት የላቸውም፡፡ልዩነት ካለ የየድርጅቶቹ ሊቀመንበሮች የየግል ፍላጎት ብቻ ነው፡፡የብዙዎቹ ድርጅቶች መኖር ለሊቀመንበሮቹ መጠሪያ ከመሆን ያለፈ ይሄ ነው ተብሎ ሊጠቀስ የሚችል ውጤት አለማስመዝገባቸውን አባላቱም የሚከራከሩበት አይደለም፡፡ ስለሆነም በየቤታቸው ግልጽ ነጻና ድፍረት የተላበሰ ውይይት በማድረግ ምን ሰራን; ምን እየሰራን ነው; ወዴትስ እየሄድን ነው; በማለት ራሳቸውን መመርመር ቀጣይ ጉዞአቸወንም መተለም ፡፡ ከዚህ በኋላ ደግሞ በጋራ መድረክ ተገናኝተው በአደረጃጃትም በዓላማም ተመሳሳይ ሆነን በስም ብቻ ተለያየትን ድርጅት ለመፍጠር ያበቃን ምክንያት ምንድን ነው; እስካሁንስ ወደ አንድነት እንዳንመጣ ያገደን ምንድን ነው ; ከዚህ በኋላስ ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎችን አንስተው መወያየትና የጋራ ስምምነት ላይ መድረስ፡፡
ሶስት፣ በብሄር የተደራጁ፣ በእነዚህ ድርጅቶች መካከል ያለው ልዩነት እንወክለዋለን የሚሉት ብሄረሰብ መለያየት ብቻ ነው፡፡ በየብሄረሰቡ ስም ተደራጅተው እንወክለዋልን ለሚሉት ህዝብ እስር ሞትና ስደት ምክንያት ሆኑ እንጂ የሚሉትን ነጻነት ማስገኘት ቀርቶ መብቱን ማስከበር አልቻሉም፡፡ ስለሆነም በየቤታቸው ግልጽ ውይይት በማድረግ ራሳቸውን መጠየቅ፣ በጋራ መድረክ ደግሞ ዓላማና አደረጃጀታችን አንድ ሆኖ መለያየታችን ለምን;በየግል የያዝነውን ዓላማ አቀናጅተን በአንድ ድርጅት ብንሰባሰብ ሊቀመንበሮቻችን ሥልጣን ያጡ ካልሆነ በስተቀር ጉዳት አለውን; የምንችል ተዋህደን የማንችል ትብብር ፈጥረን እንዳንታገል ምን ያግደናል፣ ብለው መክረው ያለፈውን የሚያካክስ መጪውን ትግል የሚያጎለብት ስምምነት ላይ መድረስ ፡፡
አራት፤ በአንድ ብሄረሰብ ስም የተደራጁ፤ በአንድ ብሄረሰብ ስም ከአንድ በላይ ድርጅቶችን ሲፈጠሩ፡ ብሄረሰቡን አንድ የማያደርጉ ምክንያቶች ኖረው ሳይሆን የግለሰቦች ሥልጣን ፍለጋ ነው፡፡ ስለሆነም ሀገራዊ ጉዳይ ወደሚመከርበትና እቅድ ወደሚወጣበት ጉባኤ ከመሄዳቸው በፊት ዓላማቸው አደረጃጀታቸውና እንወክለዋን የሚሉት ህዝብ አንድ ሆኖ የተለያየ ፓርቲ የፈጠሩበትን ምክንያት፣ ተለያይተው በመደራጀታቸው ያደረሱትን ጉዳት፤ ልዩነታቸውን የሚያስወግዱበትንና አንድ ሊያደርጋቸው የሚችለውን መንገድ፤ከሌሎች የብሄረስብ ድርጅቶች ጋር ምን አይነት ግንኙነት መፍጠር እንዳለባቸው ፤ ከሀገራዊ ፓርቲዎች ጋር ደግሞ አስከምን ድረስ አብረው መጓዝ እንደሚችሉ ወዘተ መምከርና ከአንድ ስምምነት ላይ መድረስ ፡፡
እነዚህ ተግባራት አስቀድመው ከተጠናቀቁ በአብዩ መድረክ ላይ የሚሳተፉ ድርጅቶች ቁጥር አነስተኛ አጀንዳውም ውስን ይሆናል፡፡ ይህም ጉባኤው ውጤታማ እንዲሆን ያስችለዋል፡፡የጉባኤው ዋና ጉዳይም የኢትዮጵያን ሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነት በማረጋገጥ ዴሞክራሲያዊ ሥርዐት መመመስረት የሚያስችል አንድ ወጥና የተቀናጀ ትግል የማካሄድ ስምምነት ላይ መድረስ ይሆናል፡፡ ይህ ሀሳብ ሲያዩት ህልም ሊመስል ይችላል፡፡ ነገር ግን የወያኔን የአገዛዝ ዘመን በማሳጠር ዴሞክራሲን በኢትዮጵያ እውን ለማድረግ ቆርጠው ከልባቸው ለሚታገሉ የማይቻል ነገር አይደለም፡፡ እንደውም ከልብ ከታሰበበትና ቀናነቱ ካለ በአጭር ግዜ መሆን የሚችል ነው፡፡
ሁሉም ድርጅቶች ተዋህደው አንድ ሊሆኑ አይጠበቅም፣ አይታልምም፡፡ አሁን የምንሰማው የድርጅት ብዛትም አያስፈልግም፡፡ ስለሆነም ከላይ ሁሉም በየቤታቸው፣ ብሎም አንድ አይነት አደረጃጀትና ዓላማ ያላቸው በቡድን፣ በሚሰሩት የቤት ስራ መሰረት መጀመሪያ ተመሳሳዮቹ ውህደት ፈጥረው የድርጅቶቹ ቁጥር በጣም ያንሳል፤ ከዛም ተቀራራቢዎቹ በመቀናጀት ጥምረት ይፈጥራሉ፡፡ በመጨረሻ በአንድነት ተባብሮ በልዩነት ተከባብሮ ለአስተማማኝ ድል የሚያበቃ ትግል ለማካሄድ የሚያስችል ግንባር ይፈጠራል፡፡
ይህ ግንባርም ትግሉን በአሸናፊነት ከመወጣት እስከ ሽግግር መንግስት መመስረት የሚያደርሰውን ሁለንተናዊ ስትራቴጂ ነድፎ አንድ ወጥ እንቅስቃሴ ያደርጋል፡፡ የግንባሩ መመሪያ በሁሉም ዘንድ ተፈጻሚ ይሆናል፡፡ግንባሩን የመሰረቱት ጥምር ፓርቲዎቸም ሆኑ የቅንጅቶቹ አባል ፓርቲዎች በየደረጃው የግንባሩን እቅድ ተፈጻሚ ከማድረግ ውጪ ተቃራኒ የሆነ ተግባር ላይ መገኘት አይኖርባቸውም፡፡
የግንባሩ አባል ያልሆኑ ድርጅቶች፤ የትብብር ምስራታው ሂደት ለማንም የኩርፊያ ምክንያት እንዳይፈጥር ሁሉንም የሚያሳትፍ መሆን አለበት፡፡ የቤት ስራቸውን መስራት ተስኖአቸው፣ ወይንም ተባብሮ የመስራቱ አላማውም ሆነ ፈቃደኝነቱ የሌላቸው ሆነው፤ ወይንም አብዛኛው ወገን የማይቀበለው ምክንያት አቅርበው ወዘተ የትብብሩ አካል ያልሆኑ ድርጅቶች ከተገኙ እኛም በመንገዳችን እናንተም በመንገዳችሁ ብለው ቢችሉ ለትብብሩ/ግንባሩ ድጋፍ መስጠት ይህ ካልሆነላቸውም ከአደናቃፊ ተግባር መቆጠብ፡፡
የየድርጅቶቹ አባልና ደጋፊ፤ የወያኔ አባላት ድርጅታቸው የሚፈጽማቸውን ኢሰብአዊ ድርጊቶች ሳይቀር አይተው እንዳላዩ ሰምተው አንዳልሰሙ ሆነው በመደገፋቸው ጭፍን ደጋፊዎች እያልን የምናወግዝ እኛስ ብለን ራሳችንን እንጠይቅ፡፡ አባል ወይንም ደጋፊ የሆንባቸው ድርጅቶች አንዳች እንቅስቃሴ ሳያሳዩ ፤ በግል የመጠናከርም ሆነ ከሌሎች ጋር ተባብሮ የመስራት ሙከራም ሳያደርጉ የግለሰቦች መጠሪያ ብቻ ሆነው አመታት ሲያስቆጥሩ ለምን ብለን ሳንጠይቅ መደገፋችን፣ በተግባር እንያችሁ አለማለታችን ይባስ ብሎም ለምንደግፈው ድርጅት ጥብቅና ቆመን ሌሎችን ማውገዝ ማጥላላታችን ጭፍን ደጋፊ አያሰኝም;
እናም ከዚህ እንውጣ፣ ከድርጅቶቹ ጋር ያስተሳሰረንን ሰንሰለት እንመርምር፣ግንኙነታችን የዓላማ ይሁን፤ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን የማየት አለያም ለልጆቻን የማቆየት ዓላማ፡፡ እናም አባልም ሆነ ደጋፊ የሆንባቸው ድርጅቶች ለዚህ ዓላማችን እውን መሆን በጽናት የሚታገሉ እንዲሆኑ እናግዝ፣ እናበረታታ፤ ሳይሆን ሲቀር እንጠይቅ፣ መልስ ስናጣ ደግሞ እንቃወም፤ድጋፋችንንም አባልነታችንንም እንሰርዝ፡፡ ከእንግዲህ በተግባር ስለሚታይ እንጂ በቃል ስለሚነገር ትግል ድጋፍ አንስጥ፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ከወያኔ አገዛዝ የሚገላገልበት አለያም አገዛዙ ተጠናክሮ የሚቀጥልበት ወይንም ሕዝብ አሁን እንደምናየው ብሶቱ ብሶ በፖለቲከኞቹም ተስፋ ቆርጦ በራሱ መንገድ ትግሉን የሚቀጥልበት ወቅት ላይ ደርሰናል፡፡ ይህ የሚወሰነው ደግሞ በተቀዋሚው ተባብሮና ተጠናክሮ መታገል መቻል አለመቻል ነው፡፡ ስለሆነም ነው የድርጅቶች መተባበር ግዜ የማይሰጠው አጣዳፊ ወቅታዊ ጉዳይ የሆነው፡፡ ስለዚህ የየድርጅቶቹ አባላትና ደጋፊዎች ከጭፍን ደጋፊነት በመላቀቅ ሁሉም ድርጅቶች የየራሳቸውን የቤት ስራ በመስራት በአስቸኳይ ወደ ውህደት ወደ ጥምረትና ግንባር እንዲያመሩ ግፊት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ከእንግዲህ ከፓርቲዎቹ የምንጠብቀው ስለትብብር እንዲያወሩን፣ ወያኔ የሚገዛው በርሱ ጥንካሬ ሳይሆን በእኛ ያለመተባበር ድክመት ነው እያሉ እንዲደሰኩሩልን ሳይሆን መተባበርን በተግባር እንዲያሳዩን መሆን አለበት፡፡ ለዚህም ፈጣሪ ለሁላችንም ልብ ይስጠን፡፡
No comments:
Post a Comment