በመላው ኢትዮጵያ እየተፋፋመ የመጣው የትግል ማዕበል የማይነቀንቀው መርከብ ላይ ተሳፍረን ኢትዮጵያውያንን አንድ በአንድ እንደ አሳ ልናጠምድ መረባችንን አዘጋጅተናል ብለው የሚቃዡት እነ “ልክ አስገቢዎች” ሕዝቡ አሳው ሳይሆን እነርሱን ጭምር የተሸከመው ባህሩ መሆኑን ያውቁ ዘንድ አልታደሉምና የደንቆሮ መፈክር እያሰሙ ነው። ባህሩ ከዳር እስከዳር በማዕበል እያላተማት የወያኔ መርከብ መልህቅ መጣያ ያጣች መርከበኞቹም እርስበርስ እየተናቆሩ እየተደናበሩም የመጣላቸውን አጸያፊ አባባል እየተጠቀሙ ባህሩን መራገም ቀጥለዋል። ከማዕበሉ ስለመትረፋቸው ግን የሚያውቁት ነገር የለም።
ትኩረታችን ግን ግርግሩ በሚያስነሳው አቧራ ላይ ሳይሆን መሰረታዊና አስተማማኝ ድል በሚያስገኘው ጎዳና ላይ ሊሆን ይገባልና የዛሬው ጽሁፍ የሚያጠነጥነው እኛ ስንጠቃ እነ እንትና ምንም አላሉም በሚል ስሞታና ኩርፊያ ሳቢያ ከዋናው የትግል ጎዳና ፈቅ እንዳንል በሚለው ማስገንዘቢያ ላይ ነው።
ጠላትን ለማሸነፍ ምን እያደረገና እያቀደ መሆኑን ማወቅ አስፈላጊ የሆነውን ያህል መለስ ብለን እኛስ ምን እያደረግን ነው ብለን እራሳችንን ስንገመግምና ከልምድም ስንማር ነው ለአፀፋው መዘጋጀት የምንችለው። ከመልካም ድርጊቶቻችን ብንጀምር የፖለቲካ መሪዎቻችን እንመራሀለን ከሚሉት ህዝባችን የረጅም ጊዜ አብሮ ተሳስቦ የመኖር ልምድና ፍላጎት ተምረው በእርግጥ ያሉትንም ሆነ ለፖለቲካ ፍጅታ ሲባል ብቻ የፈጠሩትን ልዩነቶች ለማስወገድ በህብረት ሲሰሩ ማየት ጀምረናል። የሁላችንም ችግር ምንጩ አንድ ነውና በጋራ እየጨለፍን እናድረቀው በማለት አብረው ሲሰሩ አበጃችሁ ግፉበት የሚባል ነው።በአንጻሩ ደግሞ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የምንሰማቸው ለችግሬ አልደረሳችሁልኝም የሚሉ ቅሬታዎች አሉ።
ኦርሞዎቹም ሆኑ ሌሎች ኢትዮጵያውያን “ኦሮሞዎች ላይ አስከፊ በደል ሲደርስ – ሲታሰሩና ሲገደሉ አማራዎች ዝም ብለዋል” ብለው ሲያማርሩ ይሰማል። ይህን ያክል የኦሮሞ ልጆች እንቅስቃሴ ሲያደረጉ ሌላው ዝምታን መርጧል የሚሉ ስሞታዎች ከየመድረኩ ይደመጣሉ። ይበልጡን ደግሞ እንደነ ተስፋዬ ያሉ ስንጥቅ አስፊ ሾተላዮች አጋጣሚውን በመጠቀም የመከፋፈል ተልዕኮአቸውን የሚያሳኩ መስሏቸው የክፋት መርዝ መርጨት ቀጥለዋል። እንደ እውነቱ ከሆነ በወገኖቻችን ላይ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በደል ሲፈጸም ዝምታን የመረጥነው ዛሬ ብቻ አይደለም። ይህ ሀቅ ሊነገር ይገባል። ሁላችንም በዚህ ተወቃሾች ነን ስህተት መስራታችንን ልንቀበል ይገባል። ይህን ሳናደርግ ከቀረን አሁንም ተራ በተራ ለሚገሉን ጠላቶች ተመቻችተን ሽንፈትን ተቀብለን ለማለቅ መርጠናል ማለት ነው።
እስኪ እራሳችንን እንዲህ ብለን እንጠይቅ፡ በርካታ አኝዋኮች ሲገደሉና ከቀዬአቸው በግፍ ሲፈናቀሉ ምን ብለናል? አማራው “ነፈጠኛ” እየተባለው ወደገደል ሲወረወር፣ ተጋብቶ ተዋልዶ ከኖረበት አካባቢ ባዶ እጁን በአንድ ጀንበር ሲባረርና ሲጨፈጨፍ ምን አድርገናል? አፋሩ መሬቱን መዝረፍ በፈለጉ ወያኔዎች ጥይት ሲቆላ ምን ፈይደናል? ኦጋዴን በወያኔ የተገደሉ ወገኖቻችን ሬሳ ክብር ተንፍጎት ሜዳ ላይ መጣል ብቻ ሳይሆን ወያኔ ለገደለበት ጥይት ካሳ ሲጠይቅ ምን አድርገን ነበር? ገዳማትን እያቃጠሉ የጫት ማሳ ሲያደርጉና “ኦርቶዶክስንና አማራን ድራሹን አጠፋነው” ብለው የባንዳ ልጆች ሲደነፉ የተቀረነው ምን አደረግን? የሚደነቅ ሰላማዊ ትግል ያደረጉ የእስልምና ሀይማኖት መሪዎች በግፍ ሲታሰሩስ ሌሎቻችን ምን ያህል ተባበርን? በኢትዮጵያ ምድር በዚህ ዘረኛ ስርዓት ያልተጠቃ አንድም ጎሳ ሆነ መንደር የለም። ስለዚህ እኛ ለወገን ያልደረስንበትን ጊዜ እንቁጠር ካልን ዝርዝሩ ማለቂያም አይኖረውም ። አንድ ላይ ስላልቆምን ነጣጥለው አጠቁን። ቁም ነገሩ እዚህ ላይ ነውና ከስሞታ አዙሪት መውጣትና ትናንት ማድረግ የተሳነን ዛሬ አድርገን እናሳይ። ፍንጩ እየታየ ነው ሁሉም ጠላቱን እየለየ አብሮነትና አንድነት በኢትዮጵያውያን ዘንድ ደምቆ መታየት ጀምሯል። ይህ ሲያስደስተን ጠላትን ክፉኛ ያስፈራዋል። እነዚህ ተጠቅመናል የሚሉት ጀሌዎቹ የዛሬ አትራፊዎችም አንኳ ቢሆኑ ዛሬ በወያኔ እንደ ውሻ ተኙ ሲሏቸው የሚተኙ ጃስ ሲሏቸው የሚጮኹ ነገ ደግሞ አንገታቸውን ቀና አድርገው መሄድ የማይችሉትም መርበድበድ ጀምረዋል።
ከምቾት ቀጠናችን ላይ ሆነን የሌላውን በደል አይቶ እንዳላየ ካለፍን መከራው ወደኛ ሲመጣ አብሮን የሚቆም ይጠፋል። እንዲያም እንኳን ሆኖ ለመሆኑ በየትኛው የሀገራችን መንደር ነው ሕዝቡ በሰላም ወጥቶ የሚገባ የተቃውሞ እንቅስቃሴ የሌለበት ብለን ስንጠይቅ ሀገሪቱ በወራሪ ሀይል ተሰንጋ መያዟንና ትንቅንቁ እንደ አቅሙና አደረጃጀቱ እዚህም እዚያም መኖሩን እንረጋግጣለን። በጎሳና አካባቢ ተሸንሽነን “እኛና እነሱ” የሚለውን ስሜት አስካራመድን ድረስ እንደ ሕዝብ እንደ ሀገር ይህንን የወንበዴ ጥርቅም ከትከሻችን ላይ አሽቀንጥረን መጣል አንችልም። ከቻልንም ብዙ መስዋዕትነት ያስከፍለናል። በትንሽ መስዋዕትነት ፈጣንና አስተማማኝ ድል ለማግኘት ግን ሌሎቹ ሲጠቁ እኛ ምን ስላላደረግን ነው አሁን ለጥቃት የተጋለጥነው ብለን መጠየቅና ፈጥኖ ለትብብር መንገዱን ማመቻቸት መፍትሄ ይሆነናል። ትኩረታችን አብረውን አልታገሉም ብለን በምንከሳቸው ላይ የምናሰማቸው ቅሬታዎችና ስሞታዎች ላይ ከሆነ ወደሚገድለን የጋራ ጠላታችን የሚያነጣጥረው እይታችንን ጋርደው እርስበርስ እንድንናከስና እንዲያውም የወያኔን ከፋፋይ ዓላማ አስፍጻሚ እንድንሆን ሊያደርጉን ይችላሉ።
ያኔ ገና ከጅምሩ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ላይ ጥቃት ሲነጣጠር “ይህ ነገር አይሆንም” ብለን በጋራ ተነስተን ቢሆን ይህ ዛሬ የምናየው ውርደትና ሰቆቃ ይመጣ ነበርን? የሀገር ጥፋትና አፍራሽነት ጥንስሱን ባለማወቃችን ወይም በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ተጠቃሚ ነን ብለን በመገመታችን ዛሬ ተራ በተራ እንድንጠቃ አላደረገንምን? ብለን ስንጠይቅና ምላሹን ስናገኝ ያኔ ወደ ድል እንደረደራለን። እነዚሁኑ የሀገር መዥገር የሆኑ የክፋት ፍሬዎችን ለመፋለምና ለሀገር ሉዐላዊነትና ክብር የወደቁ ሰማዕታትን ደም አርክሰን “ከእንግዲህ ወዲያ የኦሮሞ ልጆች ጦር ሰብቀው ወደናንተ አይመጡም” ያሉ መሪ ነን ባዮች ዛሬ የኦሮሞ ልጆች በየመንደራቸው ያልቁ ዘንድ አስተዋፅኦ አላደረጉምን? በነፃነት ትግል ስም አስነዋሪ ባርነት ውስጥ እንገባ ዘንድ አላደረጉንምን? ይህ አዙሪት ነፃ ወጣን ባሉት ዘንድስ አልቀጠለምን? ነጻ ወጣን ባሉት ወገኖቻችን ዘንድ ዛሬ ነጻነት አለን? ብለን ስንጠይቅ የተጠቃውና የተዋረደው ኢትዮጵያዊነት መሆኑ ገዝፎ ይወጣል። ተራራ አንቀጠቀጥን ባሉት የትግራይ ነጻ አውጪዎች ግዛት ዛሬ ተንቀጥቃጩ ተራራው ሳይሆን የትግራይ ሕዝብ ራሱ አይደለምን? ስለዚህ አምባገነንነትን ስንታገል የምንፋለመው የጨቋኙን የዘር ሀረግ ሳይሆን ጭቆናውን ሊሆን ይገባል። ያኔ መጠራጠርና መፈራራት አይኖርም። ያኔ እናንተና እኛ አንልም አገሮች የጋራ ግንባር ፈጥረው ጠላት የሚሉትን ሲያጠቁ የአንድ ሀገር ልጆች ተባብረው ማሸነፍ ያለመቻላቸው የጠላትን ሃያልነት ሳይሆን የኛኑ ልፍስፍስነት የሚያሳይ ነውና እጅ ለእጅ ተያይዘን ከመከራ አዙሪት መውጣት የኛው ድርሻ ነው።
ሌላ ትኩረት ሊሰጥበት የሚገባ የአነጋገር ዘይቤም አለ ምሁራን ከማለት ይልቅ “የአማራ ልሂቃን” የሚልና ወቀሳውን ወደዚያው 25 አመት ሙሉ አሳሩን የሚያየው አማራው ጋ መልሶ ለመወርወር የሚዳዳ ይመስላል። ጠለቅ ብሎ ላልተመለከተው ቀላል ቢመስልም የኦሮሞ ምሁራንስ ምን አደረጉ ከተባለ ሌላ ስንጥቅ ማበጀት ይሆናል። ዘር ሳይመርጥ ለጠቅላላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነጻነት የሚታገል ከሆነ ልክ እንደ ወያኔ ኢትዮጵያ የሚሉ ሁሉ አማሮች ናቸው ብለን ደምድመን እንዳይሆን ያስፈራል። በሌላ በኩል በአማርኛ ጥሩ የሚጽፉና የሚናገሩ ምሁራን ሁሉ የግድ አማራ ናቸው ብሎ መደምደም ስህተት ነው። ራሳቸውን አማራ ነኝ በአማራነቴ እወቁኝ ብለው ካላስተዋወቁና ለአማራው ብቻ ቆሜአለሁ ካላሉ ስለምን ጥያቄው ይነሳል? የዘር ግንዱ አማራ ወይም ኦሮሞ ወይም ሌላ የሆነ ኢትዮጵያዊ ራሱን በኢትዮጵያዊነት እንጂ ማንነቱን በጎሳው የማይገልጽ ምሁር በርካታ አይደለምን? ለመሆኑ ዛሬ በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ በህዝባችን ላይ የሚደርሰውን በደል የሚዘግቡት ጋዜጠኞች፣ በሰላማዊ ሰልፎች ላይና በግንባር መሳርያ ይዘው የሚፋለሙት ወገኖቻችንን በዘር ለይተን እናውቃቸዋለን? ጉዳዬ ብሎ ዘራቸውን የሚቆጥርስ ማነው?
በመጀመርያ በነጻነት ስም በክልል ስንካለልና በወያኔ ሴረኞች የተጫነብንን የአፓርታይድ ክልል እንደመልካምና ልንለወጠው እንደማንችለው ነገር ተቀብለን ስናስተጋባ ኪሳራ ውስጥ ገብተናል። በክልል መታቀብ ማለት በግልጽ እስር ቤት መግባት ማለት ነው። እንቅስቃሴው በኪሎሜትር ተገድቦለት ከዚህ ኪሎሜትር አልፈህ ብትገኝ ተብሎ የሚታቀብ እስረኛ ነው። በካናዳ አሜሪካና አውስትራልያ የሀገሬው ነባር ሕዝብ በክልል (ሪዘርቭ) ተገድቦ መጤዎቹ ነጮቹ ባዘጋጁት የትምህርት ስርአት እንዲማርና ቋንቋውንም እንዳይናገር ከተከለለበት ስፍራ ውጪ እንዳይንቀሳቀስ ተደርጎ በመሰቃየቱና አእምሮው በመጎዳቱን ዛሬን ድረስ ጤነኛ ሕይወት የማይመሩት ይበዛሉ። ሲጋራ አደንዛዥ እፅና አልኮል መጠጥ በትንሽ ክፍያ እንዲያገኙ እየተደረገ በ እግራቸው የማይቆሙ ማንነታቸወን የረሱ እንዲሆኑ ተደረገዋል። ተመሳሳይ ስራ በወያኔ እየተደረገ ነው ሁሉም መጥፎ ነገሮች ከትግራይ ክልል ውጪ እንዲሆኑ በማድረግ ትውልድ የመግደል ስራ እየተሰራ ነው። የ አንድ ሀገር ሕዝብ የጋራ ቋንቋ አንዳይኖረው ያደረገው ክልላው አስተዳደር ነው።፡ በኢትዮጵያ በክልል ስም የሚደረገውም ግፍም አብሮ የኖረን ሕዝብ አንተ በክልልህ እየተባለ በገዛ ሀገሩ ተዘዋውሮ ሰርቶ እንዳይበላ ተደርጓል። ባልና ሚስት እስከመለያየት ድረስ ግፍ ሲፈጸም የትግራይ ሹማምንት ልክ እንደ ነጮቹ ወራሪዎች በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች አድራጊና ፈጣሪዎች ሆነው ኖሩ። ኢትዮጵያዊነትን ከፍ አድርገን ይህንን መሰሪ የክልል ድር መበጣጠስ ይኖርብናል። አማራና ኦሮሞ ቢጋቡ ጎንደርና ባሌ መኖር የማይችሉበትን ስርዓት ተቀብሎ መኖር ውርደት ነው። ይባስ ብሎ የሁለቱ ልጆች ደግሞ አገር አልባ ናቸው። ልጆቹን አገር የሚያሳጣ ወላጅ ደግሞ ሁለቴ የሞተ ነውና አንዴ ሞቶ አገር ቢያድን ታሪክም ትውልድም ሲያነሳው ይኖራል። ዛሬ ከምንጊዜውም በላይ በተለያዩ የሀገሪቱ ጎሳ አባሎች ደምና አጥንት የተገነባችውን ኢትዮጵያ የነጻነት አየር የሚነፍስባት ትልቅ አገር እናደርጋት ዘንድ በጋራ እንነሳ።
No comments:
Post a Comment