Sunday, January 17, 2016

ያለ አንድነት ስለ አንድነት

ስለ አንድነት ብዙ ጊዜ ይወራል ። አንድነት ስንል ግን ምን ማለታችን ነው ? አንድ ላይ እንስራ እና አንድ ሆነን እንስራ በሚሉት ሃሳቦች መሃከል ውስጥስ ያሉትስ ልዩነቶች ምንድን ናቸው ? የአንድነት ኃይሎች ፣ እንደ’ሚታሙት (እንደሚባሉት) ፣ “አንድነት” የሚለውን ሃሳብ ለ -ፖለቲካ ግብዓትነት ነው የሚጠቀሙበት ወይስ የአንድነትን ጥቅም ስለተረዱ ነው ሃሳቡን የሚያቀነቅኑት ? የአንድነት ኃይሎች ስለመሆናቸው ማሳያውስ ምንድን ነው ? አረጓዴ፣ ብጫ እና ቀይ ቀለም ያለው የሀገራችንን ሰንደቅ በመሸከማቸው ? ስለ በላይ ዘለቀ ፣ አሉላ እና ቴዎድሮስ በመስበካቸው ? ስለ ላሊበላ አክሱም እና የሐ በመዝፈናቸው ? አንድነት መገለጫው ምንድን ነው ?
ለምሳሌ እኔ የታዘብኩትን ነገር ላስቀምጥ ። ሕወሓት ከመፈጠሩም -በፊት የትግራይ ሕዝብ በ-አሉላ እና በ-አጼ በዮሃንስ ይሸልል ነበር ፣ ዘፈኖቹ በአብዛኛው የነዚህን ሰዎች ስሞች እየጠቀሱ የሚዘፈኑ ነበሩ ፣ አሁን በጣም ቢመናመኑም አልሞቱም ፣ ዛሬም አሉ ! ወደ ጎንደር ስንወርድ ያለው ነገር ያው ነው ፣ ቴዎድሮስ እና ፋሲል ነው የሚባለው ፣ የልጆቻቸው ስም የሚያንጸባርቀውም እሱኑ ነው ፣ ” ቴዎድሮስ ” ፣ ” ፋሲል” ” ሸዋን ግዛው ” እና ወዘተ ። ወደ ጎጃም ስትሄድ ደሞ ” ድሮም የበላይ ነኝ ” ነው የሚለው ዘፈኑ ። በሚኒሊክ ጀግንነት ላይ አንዳች ልዩነት የሌለው ጎጃሜ ፣ ” ጥንትም የበላይ ነኝ ” ወይም ” “እኔ የበላይ ዘር” ባለበት አንደበቱ ” ጥንትም ያሉላ ነኝ ” ወይም ” እኔ የሚኒልክ ዘር” ብሎ ሲዘፍን አይተን አናውቅም ። ወደ ሸዋም ስትወርድ እንዲሁ ነው ። < አንኮበር የሚኒልክ ሀገር> እየተባለ ይዘፈናል ፣ < ትግራይ የ አሉላ ሀገር > ተብሎ ሸዋ ውስጥ ሲዘፈን የማስታውሰው ነገር የለም ። እኔ እስከማውቀው ድረስ ። ወሎም ከዚህ የተለየ ነገር የለም ፣ የወሎ ሰዎች ስለ ንግስና ሲያወሩ ወይም ሲጫወቱ ዛሬም ስለ ልጅ እያሱ አገዳደል መጫወቱ ይቀላቸዋል ። ተጋዳላዮች ፣ ዛሬም በየ ቡና ቤቱ ስለ ደርግ እንደሚያወሩት ማለት ነው ። የጅማ ኦሮሞዎች ስለ አባ ጅፋር ብዙ ዘፍነዋል ፣ ከጅማ ስለ ሚኒሊክ ፣ በአባ ጅፋር ቅላጼ ፣ ፍቅር መጠበቅ በአሁኑ ሰዓት እጅግ አስቸጋሪ ነው የሚለው ብቻ የሚገልጸው አይመስለኝም። ባሌ-ጎባም እንዲሁ ነው ። ወለጋም ያው ነው ። ይህንን ነባራዊ ሁኔታ በትክክል ለሚያጤን ጤነኛ ሰው፣ < አንድነት ማለት ምን ማለት ነው?> ለሚለው ጉዳይ ትክክለኛ መልስ ይኖረዋል ብዬ አልገምትም ። እንደገባኝ ግን በኢትዮጵያ ታሪክ አንድነት ማለት ስለ ራስ ብቻ እየዘፈኑ ስለ ሌሎችም ያገባኛል ማለት ይመስለኛል ። ከማየው እና ከተረዳሁት ፣ አንድነት ብለን ስንሰብክ ፣ ባንደበታችን ኢትዮጵያዊ ስንሆን በልቦናችን ግን ትግሬ ብቻ ነን ፣ ጎንደሬዎች ብቻ ነን ፣ ጎጃሜዎች ብቻ ነን ፣ ወሎዬዎች ብቻ ነን ፣ የሸዋ ሰው ብቻ ነን ፣ ኦሮሞዎች ብቻ ነን ፣ ጉራጌዎች ብቻ ነን ፣ ሀደሬዎች ብቻ ነን ፣ ዶርዜዎች ብቻ ነን ። ለዚህ ደሞ ብዙ ማሳይዎች አሉ ። ለምሳሌ አንድ የታወቀ ጎጃሜ ሲሞት ፣ መጀመሪያ ለ ጎጃምነቱ ነው ደረት የሚመታው ፣ ኢትዮጵያዊነቱ የሚመጣው ከዚያ ቀጥሎ ነው ። አንድ ጎንደሬ ዘፋኝ ሙዚቃ ሲያወጣ መጀመሪያ ለጎንደሬነቱ ነው ወሬው የሚራገብለት ፣ ኢትዮጵያዊነቱ ሁለተኛ ወይም ሶስተኛ ነገር/ ጉዳይ ነው ። ለኦሮሞውም እንዲሁ ነው ፣ ለሸዋውም ያው ነው ። የትግሬው ትንሽ የተጋነነ የሚመስለው ፣ አደረጃጀቱም ፣ መዋቅሩም ፣ አሰራሩም ሙሉ በሙሉ ዘርን መሰርት ያደረገ ስለሆነ ነው እንጂ እውነቱን ለመናገር ሁሉም አንድ አይነት ነው ። አይንድ አይነት ባይሆን ኖሮ ፣ ትግሬ ብቻውን የተለየ ባህሪ ይዞ መጥቶ ፣ ይህንን ሁሉ ሕዝብ ረግጦ መግዛት ባልቻለ ነበር ።
ለዚህ ነው ጎረምሳ ና ዘረኛ ( ጎሳ ተኮር ) ፖለቲከኞች ፣ ባንድ መንፈቅ –ሺ ተከታዮችን የሚያፈሩት ፣ልባቸው በትዕቢት የሚሞላው እና የሚያብጠውም ፣ የመሃብረሰባችንን ስነ ልቦናዊ የማንነት አወቃቀር በደንብ ስለሚረዱት ይመስለኛል ።
ፖለቲከኞቻችን ( ወይም አሁን ባለው ሁኔታ ቧልተኞቻችን ) ፣ < የጋራ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ > የሚሏት ጥራዝ ነጠቅ አስተሳሰብ አለች ። በመጀመሪያ የጋራ ማለት ምን ማለት ነው ፣ ቁንጽል የጋራ ? ግማሽ የጋራ ? እሩብ የጋራ ? የሚባሉ ነገሮች አሉ ወይ ። የጋራ በሆኑ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ አብረን ለመስራት ተስማምተናል ስንል ፣ አንድ ሞኝ የጋራ ባልሆኑትስ ብሎ ሊጠይቅ ይችላል ። ዋናው ጥያቄ ግን የጋራ የሆኑት ጉዳዮች ፣ የጋራ ከማያረጉን ጋ ሲወዳደሩ ፣ ለጋራ ጉዳዮች አብሮ ከመስራት የጋራ ባልሆኑ ጉዳዮች ላይ መጣላት የተሻለ ሊሆን ይችላል ። ( የተሻለ ነው አላልኩም !)።
ወይም አብሮ መስራቱ ምን ማለት እንደሆነ እንዴት እንዳልገባን ላስረዳ ።
ለምሳሌ ድርጅት ሀ እና ድርጅት ለ የጋራ የሚያደርግ የፖለቲካ ጉዳይ አላቸው እንበል ። ይህም የፖለቲካ ጉዳይ ድርጅት መ’ን ማስወገድ ሊሆን ይችላል ። ግን ድርጅት ሀ የራሱን ክልል መስርቶ መኖር ይፈልጋል ፣ ድርጅት ለ ደሞ ሀገር አንድ አድርጎ ማስተዳደር ይፈልጋል ። ድርጅት ለ ድርጅት መ ወድቆ ድርጅት ሀ የራሱን ክልል ልመስርት ቢል እንቢ ማለት አይችልም ። ምክንያቱም አብረው የሰሩት ድርጅት ሀ የራሱን ክልል እንዳይመሰርት ሳይሆን ድርጅት መ’ን ለመጣል ብቻ ነው ። ከዚህ ባለፈ ብዙ ውስብስብ የሆኑ ጉዳዮች አሉ ። በዘር ላይ የተደራጁ የፖለቲካ ድርጅቶች ትልቅ የሚያደርጋቸውም በዘር መደራጀታቸው ብቻ አይደለም ። ዘረኛ ተከታዮችም ስላሏቸው ጭምር እንጂ ! ለምሳሌ ወጣት መ ብቻውን አንድ ሰው ነው ። መ’ን ትልቅ ያደረገው ግን የሱ አይነት አመለካከት ያላቸው ብዙ ሺዎች ስለሚከተሉት ነው ። ችግር ከተባለ ፣ ችግሩ መ ላይ ሳይሆን፣ የተከታዮቹ ላይ ነው ያለው ማለት ነው ።
ይህንን ሳስብ ነው < አንድ ሆነን አናውቅም አንድ ላይ ግን ኖረን እናውቃለን> ፣ ብዬ ለማለት የምደፍረው ።
የወያኔ ጭካኔ ፣ ዘረኝነት እና ሌሎችም ገልጸን የማንጨርሳቸው ጉዳዮች ዛሬ ሀገራችን ያለችበትን እውነታ ይገልጽ ይሆናል ። ግን እውነታ ስለሆነ ችግሩ ምን እንደሆነ ታውቋል ማለት አይደለም ። ሜርሊን ሮብርሰን ” Fact explains nothing, in the contrary it is fact that requires explanation ” ትላለች ። እውነታ አንዳች የሚገልጸው ነገር የለም ፣ ይልቅስ እውነታው ነው ማብራሪያ የሚያስፈልገው ” እንደማለት ነው ። ጸሓይ ትሞቃለች ( ወይም ታሞቃለች ) እውነታ ነው ፣ እውቀት እና እውነቱ ግን ያለው ለምን ትሞቃለች ( ወይም ታሞቃለች ) የሚለው ላይ ነው ። ወያኔ የሚገዛን አንድ መሆን ባለመቻላችን ነው የሚለው አርፍተ ነገር እውነታ ነው ፣ ለምን አንድ መሆን አቃተን የሚለው ግን እውነታውን የሚያብራራ እውቀት ነው ። ጥያቄው < እንድ እንሁን > አይመስለኝም መሆን ያለበት ፣ ጥያቄም መሆን ያለበት እንዴት አንድ እንሁን የሚለው ላይ ነው ። በዘር ፣ በቋንቋ ፥ በመልካ-ምድር እና ወዘተ መለያየቱ አይመስለኝም አንድ እንዳንሆን ያገደን ፣ ወይም አንድ ከሆንን ወዲያ በአንድነት እንዳንቆም እንከን የሆነብን። ለኔ ችግሩ ያለው የትራክተር ጎማ ፣ የቤቢ ፊያት ኢንጅን ፣ የዔነትሬ ማርሽ አንድ ላይ ገጣጥመን ሀገር የምትባል መኪና ሰርተናል ማለታችን ላይ ነው ። የጋራ የሚያደርጉን ሃሳቦች ሲገጣጠሙ የሚሰሩት የተጣመሙ ነገሮችን ብቻ ነው ፣ ምክንያቱም የቆምንበት መሰረት የኛን ሚዛን ብቻ እንዲሸከም ሆኖ የተሰራ ነውና ።
ታዋቂው ገጣሚ ስፔናዊው አንቶኒዮ ማቼዶ
“wanderer, there is no path,
the path is made by walking.”
“ኳታኞች፣ ምህዋር የለም
ምህዋር በእርምጃ ነው የሚሰራው !” ይላል ።
ስለዚህ ስለ አንድነት ስናወራ
ኳታኞች በመንደርተኝነት መስረት ላይ የቆመ ሀገር የለም !
ሕዝብ ሆይ በፊርማ እና በቅስቀሳ የሚመጣ አንድነት የለም ፣ በስምምነት እና በወረቀት የሚገኝ ህብረተሰባዊነት የለም ፣ አንድነት አብሮ በመኖር ነው የሚመጣው ፣ እሱን ለማምጣት መጀመሪያ ራሳችንን ከራስችን ውስጥ ማስወጣት !

No comments:

Post a Comment